እግዚአብሔርን ማወቅ- ክፍል …..3…..
የእግዚአብሔር ባሕርያት
ስለእግዚአብሔር ለማወቅ ፍንጭ የሚሰጡን፣ የሚገልጡት ባሕርያቱ ናቸው።
መገለጫዎቹ፡-
፩. አይታይም፡- እግዚአብሔር ረቂቅ – መንፈስ ነው። ደቃቅ ሆኖ በአጉሊ መነጽር /በማይክሮስኮፕ/ ወይም ሩቅ ሆኖ በርቀት – መነጽር /በቴሌስኮፕ/ የሚታይ አይደለም።
– « ብቻውን አምላክ ለሚሆን ለማይጠፋው ለማይታየውም ለዘመናት ንጉሥ ምስጋናና ክብር እስከ ዘላለም ድረስ ይሁን፤ አሜን።» ፩ ጢሞ ፩፣ ፲፯
o በስሜት ሕዋሳቶቻችን ልንደርስበት አንችልም።
o ከምናውቃቸው በመጀመር የርቀት /የመርቀቅ/ ቅደም ተከተል ሲቀመጥ ፡ ከግዙፍ ወደ ረቂቅ፡-
o እግዚአብሔር የማይታይ እንጂ የማያይ አይደለም።
o በእምነት ግን በሕይወታችን እናየዋለን።
፪. አይወሰንም፡- በስፍራ/በቦታ የተወሰነ አይደለም። በዚያ አለ፤ በዚህ የለም፤ ይሄዳል/ይመጣል… አይባልም።
– «ከመንፈስህ ወዴት እሄዳለሁ? ከፊትህስ ወዴት እሸሻለሁ?
ወደ ሰማይ ብወጣ፥ አንተ በዚያ አለህ። ወደ ሲኦልም ብወርድ፥ በዚያ አለህ።
እንደ ንስር የንጋትን ክንፍ ብወስድ፥ እስከ ባሕር መጨረሻም ብበርር፥
በዚያ እጅህ ትመራኛለች፥ ቀኝህም ትይዘኛለች።» መዝ ፻፴፱/፻፵፣ ፯ – ፲
o በሁሉም ቦታ አለ። ይህ ሲባል ግን በየቦታው ያሉት ነገሮች ሁሉ ግን የእርሱ አካል ናቸው ማለት አይደለም።
፫. አይለወጥም፡- በጊዜ ተጽእኖ ሥር አይደለም። ሁሉም ነገሮች በጊዜ ብዛት ይለወጣሉ፣
– «…. ደግሞ። ጌታ ሆይ፥ አንተ ከጥንት ምድርን መሠረትህ፥ ሰማዮችም የእጆችህ ሥራ ናቸው፤ እነርሱም ይጠፋሉ አንተ ግን ጸንተህ ትኖራለህ፤ ሁሉም እንደ ልብስ ያረጃሉ፤ እንደ መጎናጸፊያም ትጠቀልላቸዋለህ ይለወጡማል፤ አንተ ግን አንተ ነህ፥ ዓመቶችህም ከቶ አያልቁም» ዕብ ፩፣ ፲ – ፲፪
o ጊዜ/ዘመን ሁሉንም ያስረጃል። እግዚአብሔር ግን ዘመንን ራሱን ያስረጀዋል።
o እግዚአብሔር ብሉየ-መዋዕል፡- የተባለው በግዕዝ – ዘመናትን የሚያስረጅ ማለት ነው።
o እግዚአብሔር የሚያልፍበት ወይም የሚጠብቀው ጊዜ የለም። ትናንት/ነገ – የዛሬ ዓመት የሚቀጥለው ዓመት.. የሚባል የለም። በእርሱ ዘንድ ሁልጊዜ ዛሬ ነው።
«ያለውና የነበረው የሚመጣውም ሁሉንም የሚገዛ ጌታ አምላክ። አልፋና ዖሜጋ እኔ ነኝ ይላል።» ራእ ፩፣ ፰
o ሰው ሊገዛ/ ሊቆጣጠር የሚችለው ያለውን /የአሁኑን/ ብቻ ነው። ለዚያውም የሚታየውን እና የቻለውን ያህል።
o እግዚአብሔር ግን ያለውን፡ የነበረውን/ያለፈውን/ የሚመጣውንም ሁሉ ይገዛል፤ ይቆጣጠራል፣ ያስተዳድራል።
o በእኛ ዘንድ ሺህ ዓመት በእግዚአብሔር ዘንድ እንደ አንድ ቀን ነው ሲባል እግዚአብሔር የሺ ዓመቱን ሥራ ዛሬ እንደተደረገ ያህል ነው – በዝርዝር የሚያውቀው። እኛ እንረሳለን።
o እግዚአብሔር ስለማይለወጥ ስለእርሱ በትክክል የገባን ነገር አይለወጥም። ያው ነው ማለት ነው። ስለእርሱ በእርግጠኝነት መናገር እንችላለን። እንዲህ ነው ብለን።
ስለ ሰው ግን እገሌ እንዲህ ነው ብለን በእርግጠኝነት መናገር አንችልም ፣ ሰው ይለወጣልና።
– እግዚአብሔር ስለማይለወጥ ዘላለማዊ ነው፣
o የነበረ፣ ያለ ፣ የሚኖር ነው። ለሙሴ እንደተናገረው። – እግዚአብሔርም ሙሴን፦ «ያለና የሚኖር» እኔ ነኝ አለው፤ ዘፍ ፫፣ ፲፬
፬. አይከፋፈልም፡ ሰው በሁለት ይከፈላል – ነፍስና ሥጋ ። ሰውነቱ/- ከአጥንት፣ ከደም፣ ከሥጋ የተሠራ ነው። ነፍሱ የእግዚአብሔር እስትንፋስ ሆና መንፈስ አለው፤
o እግዚአብሔር ግን ከዚህ እና ከዚህ ነገሮች የተዋቀረ/የተገኘ ነው አይባልም።
o እርሱ ሁሉን ያስገኘ እንጂ እርሱን የሚያስገኙ/ያስገኙ ነገሮች የሉም።
/ይቀጥላል/…