አውቃለሁ እንደሚል ሰው የሚያስፈራ ሰው የለም፡፡ አውቃለሁ የሚል ሰው ለመማር ምንም ስፍራ የለውም፡፡ አውቃለሁ የሚል ሰው ለመማር ፈቃደኛ አይደለም፡፡ አውቃለሁ የሚል ሰው ለመሻሻል ምንም ቦታ የለውም፡፡ አውቃለሁ የሚል ሰው ማደግ አቁሟል፡፡ ሁሉንም አውቃለሁ የሚል ሰው ለመለወጥ ተስፋ የለውም፡፡
ለራሱ ጠቢብ የሆነ የሚምስለውን ሰው አየኸውን? ከእርሱ ይልቅ ለሰነፍ ተስፋ አለው። ምሳሌ 26፡12
ሁሉን አውቃለሁ ማለት የሚችል እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ ሁላችንም እየተማርን ነው፡፡ ለመማር እስከተዘጋጀን ድረስ ሁል ጊዜ እንማራለን፡፡ ለመማር እስከፈቀድን ድረስ የምንማራቸው እጅግ ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ እያንዳንዱ ሰው በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ በእውቀት ይበልጠናል፡፡ ከማንም ሰው ለመማር ፈቃደኛ ከሆንን ማንም ሰው ሊያስተምረንና በህይወታችን ላይ ዋጋን ሊጨምር ይችላል፡፡ ሁልጊዜ የሚማር ልብ ካለን በማንም ሰው አማካኝነት ለህይወታችን መለወጥ የሚጠቅም ቁልፍ ነገር ልንማር እንችላለን፡፡
ሰው ባወቀ መጠን የሚያውቀው ማወቅ የሚገባውን ያህል አንደማያውቅ ነው፡፡
ማንም አንዳች የሚያውቅ ቢመስለው ሊያውቅ እንደሚገባው ገና አላወቀም፤ 1ኛ ቆሮንቶስ 8፡2
Month: March 2021
የእግዚአብሔር መንግስት አስተሳሰብ
በምድር ላይ ህዝብን የሚያስተዳድርና የሚገዛ መንግስት እንዳለ ሁሉ በመካከላችን የእግዚአብሔር መንግስት አለ ይህም የእግዚአብሔር መንግስት የሚገለጥባት ቤተክርስቲያን ነች፡፡ የእግዚአብሔር መንግስት በአይን የማይታይ በስፍራ የማይወሰን መንግስት ነው፡፡ የእግዚአብሔር መንግስት መሪ ያለው ህዝብና የራሱ የአሰራር ህግ ያለው መንግስት ነው፡፡
ፈሪሳውያንም፦ የእግዚአብሔር መንግሥት መቼ ትመጣለች ብለው ቢጠይቁት፥ መልሶ፦ የእግዚአብሔር መንግሥት በመጠባበቅ አትመጣም፤ ደግሞም፦ እንኋት በዚህ ወይም፦ እንኋት በዚያ አይሉአትም። እነሆ፥ የእግዚአብሔር መንግሥት በመካከላችሁ ናትና አላቸው። ሉቃስ 17፡20-21
በተቃራኒው አለም ማለት ሰይጣን የሚገዛበት የአሰራር ስርአት ነው፡፡ አለም ማለት ከተማ ማለት ሳይሆን ሰው ባራሱ ላይ ጌታ የሆነበትና የሰው አስተሳሰብ የሚስተናገድበት ከእግዚአብሔር መንግስት ተቃራኒ የኑሮ ዘይቤ ነው፡፡
ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን አትውደዱ፤ በዓለም ያለው ሁሉ እርሱም የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት ስለ ገንዘብም መመካት ከዓለም ስለ ሆነ እንጂ ከአባት ስላልሆነ፥ ማንም ዓለምን ቢወድ የአባት ፍቅር በእርሱ ውስጥ የለም። 1ኛ ዮሐንስ 2፡15-16
የእግዚአብሔር መንግስት አስተሳሰብና የአለም(የሰው) አስተሳሰብ እጅግ የተለያዩ ናቸው፡፡
ዓለሙም ምኞቱም ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል። 1ኛ ዮሐንስ 2፡17
የአለም ወይም የሰው ስንል ከእግዚአብሔር ቃል የተቃረነ የአስተሳሰብ ዘይቤና ዋጋ አመለካከት ነው፡፡
የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም በጎና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም የሆነው ነገር ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ። ሮሜ 12፡2
የእግዚአብሔር መንግስት አስተሳሰብ ከአለም(ከሰው) አስተሳሰብ የሚለይበት ብዙ መንገዶች መንገዶች አሉ ከእነዚህም ውስጥ፡፡
• የፍቅርና ራስ ወዳድነት አስተሳሰብ
የእግዚአብሔር መንግስት አስተሳብ የእግዚአብሔር የሆነውንና ሰውን ሁሉ የመውደድ አስተሳሰብ ነው፡፡ ከእግዚአብሔርና ከሰው ጋር በአክብሮት የምንኖርበት ስርአት ነው፡፡ የአለም (የሰው) መንግስት ግን ራስ ተኮር የሆነ እያንዳንዱን ነገር ከግል ጥቅም አንፃር ብቻ የሚመዘንበት ስርአት ነው፡፡
እርሱ ከጨለማ ሥልጣን አዳነን፥ ቤዛነቱንም እርሱንም የኃጢአትን ስርየት ወዳገኘንበት ወደ ፍቅሩ ልጅ መንግሥት አፈለሰን። ቆላስይስ 1፡13-14
• የብርሃንና የጨለማ መንግስት
የእግዚአብሔር መንግስት በእግዚአብሔር ምሪት የተሞላ ነው፡፡ የአለም መንግስት ግን የእግዚአብሔር ምሪት የሌለበት ሰዎች መቼ እንደሚደናቀፉ የማያውቁበት የጨለማ መንግስት ነው፡፡ የእግዚአብሔር መንግስት የግልፅነት መንግስት ሲሆን የአለም መንግስት ድብቅ መንግስት ነው፡፡
ብርሃንም ወደ ዓለም ስለ መጣ ሰዎችም ሥራቸው ክፉ ነበርና ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ስለ ወደዱ ፍርዱ ይህ ነው። ክፉ የሚያደርግ ሁሉ ብርሃንን ይጠላልና፥ ሥራውም እንዳይገለጥ ወደ ብርሃን አይመጣም፤ እውነትን የሚያደርግ ግን ሥራው በእግዚአብሔር ተደርጎ እንደ ሆነ ይገለጥ ዘንድ ወደ ብርሃን ይመጣል። ዮሃንስ 3፡19-21
• የእውነትና የሃሰት አስተሳሰብ
የእግዚአብሔር መንግስት የእውነት መንግስት ነው፡፡ የእግዚአብሔር መንግስት ከእግዚአብሔርን ቃል የመጀመሪያውን የእግዚአብሔርን ሃሳብ የሚከተል መንግስት ነው፡፡ የአለም አሰራር ግን ላይ ላዩን ብቻ ማስተካከል የሚፈልግ ውስጡን ግን የማያጠራ የሃሰት ማስመሰያ አስተሳሰብ ነው፡፡ የአለም አስተሳሰብ ውጭውን ብቻ በማሳመር የሚያታልል ሲሆን የእግዚአብሔር መንግስት ትኩረቱ የውስጥ የልብ ንፅህና ነው፡፡
ብዘገይ ግን፥ በእግዚአብሔር ማደሪያ ቤት መኖር እንዴት እንደሚገባ ታውቅ ዘንድ እጽፍልሃለሁ፤ ቤቱም የእውነት ዓምድና መሠረት፥ የሕያው እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ነው። 1ኛ ጢሞቴዎስ 3፡15
• ማገልገልና የመገልገል መንገድ
በእግዚአብሔር መንግስት ባለን ነገር ሁሉ ለማገልገልና ሌሎችን ለመጥቀም የምንኖረው ኑሮ ሲሆን የአለም አስተሳሰብ በስልጣናችን ተጠቅመን ለመጠቀምና ሰዎች እንዲያገለግሉንና እንዲጠቅሙን የምንሄድበት አስተሳሰብ ነው፡፡
• የመዝራትና የማከማቸት አስተሳሰብ
የእግዚአብሔር መንግስት የመዝራትና የመስጠት አስተሳሰብ ነው፡፡ የእግዚአብሔር መንግስት ሌሎችን በመባረክና በማንሳት ቤተክርስቲያንን በማገልገል የሚረካ አስተሳሰብ ነው፡፡ በአለም ግን ሰው ደህንነት የሚሰማው ሲያከማች ሲሰበስብ ነው፡፡
ብልና ዝገት በሚያጠፉት ሌቦችም ቆፍረው በሚሠርቁት ዘንድ ለእናንተ በምድር ላይ መዝገብ አትሰብስቡ፤ ነገር ግን ብልም ዝገትም በማያጠፉት ሌቦችም ቆፍረው በማይሠርቁት ዘንድ ለእናንተ በሰማይ መዝገብ ሰብስቡ፤ ማቴዎስ 6፡19-20
• የይቅርታና የበቀል አካሄድ
የእግዚአብሔር መንግስት የምህረትና የይቅርታ መንግስት ነው፡፡ የእግዚአብሔር መንግስት በእጅጉ ይቅር የተባሉ ሰዎች በተራቸው ሌላውን ይቅር ለማለት የተዘጋጁ ሰዎች መንግስት ነው፡፡ የአለም መንግስት ግን የበቀልና የተንኮል አስተሳሰብ የገነነበት ሲሆን አንዱ በሌላው ላይ ተረማምዶ ወደላይ ከፍ የሚልበት ክፉ አሰራር ነው፡፡ በአለም አስተሰታሳብ በፊትህ የሚቆመውን አስወግደህ ማለፍ አዋቂነት ነው፡፡
• የመተባበርና የፉክክር አስተሳሰብ
በእግዚአብሔር መንግስት ለሌላው መነሳትና ማሸነፍ በደስታ የሚሰራበት ሲሆን በአለም አሰራር ግን ሌላውን በመጣል ከሌላው በላይ ከፍ ብሎ ለመታየት በትእቢት የሚኬድበት የአሰራር ዘይቤ ነው፡፡ የእግዚአብሔር መንግስት የሌላውን ጉድለት ለመሙላት የመሄድ አስተሳሰብ ሲሆን የአለም አስተሳሰብ ሌላው ሁሉ ለእርሱ እንዲሰራለት ራስን ብቸኛ እንደተመረቀ መቁጠር ነው፡፡
• ዘላለማዊና ጊዜያዊ አስተሳሰብ
የእግዚአብሔር መንግስት አስተሳሰብ የሚመዘነው በዘላለማዊ እይታው ነው፡፡ የእግዚአብሔር መንግስት ዜጋ ለዘላለም ከእግዚአብሔር ጋር እንደሚኖር የእግዚአብሔር ልጅ ጊዜያዊውን ደስታ ንቆ የሚኖረበት ህይወት ነው፡፡ የአለም አስተሳሰብ ግን ለጊዜያዊው ነገር ህይወትን የማባከን ህይወት ነው፡፡
• የትህትናና የትእቢት አስተሳሰብ
የእግዚአብሔር መንግስት መዋረድና የዝቅታን አስተሳሰብን ሲያስተምር የአለም አስተሳሰን ግን የትእቢት የከፍታ የንቀትና ትምህክትኘነትን ስግብግብነትን፣ አስተሳሰብን ያራምዳል፡፡ በአለም አሰራር ትህትና ሽንፈትና ደካማነት ነው፡፡
• የየዋህነትና የብልጠት አካሄድ
የእግዚአብሔር መንግስት አስተሳሰብ ሃይልን ለክፉ ነገር ያለመጠቀም ውሳኔ ሲሆን በአለም ግን ብልጠትና አቋራጭ ተጠቅሞ ወደላይ ከፍ ማለትን የሚያበረታታ አሰራር ነው፡፡ የእግዚአብሔር መንግስት ሰው ስለ ደህንነቱ በእግዚአብሔር ላይ የሚደገፍበት ሲሆን የአለም አሰራር ግን ባለህ ሃይል እና ተሰሚነት ሁሉ ተጠቅመህ ሌላውን በመጣልና በማዋረድ ከፍ የማለት አስተሳሰብ ነው፡፡ በአለም አንተ ከፍ እንድትል ሌሎች መዋረድ አለባቸው፡፡
ስለዚህ ነው ጌታችን ኢየሱስ የእግዚአብሔር መንግስት ቀርባለችና ንስሃ ግቡ እያለ ይሰብክ የነበረው፡፡ በአለም አስተሳሰብ በእግዚአብሔር መንግስት ሊሳካልን አይችልም፡፡
የሙታን ትንሣኤ
• የሙታን ትንሳኤ በሚመጣዉ ዓለም ከጌታ ጋር የምንኖረዉ ህይወት ነዉ (ፊል. 3፡10-11፣17-21) ፡፡ የሙታን ትንሳኤ ከሁሉ ይልቅ የተሻለ ተስፋ ያለዉ መሠረታዊ ትምህርት ነዉ፡፡
15.1. ትርጉም
• ለሰዎች ሁሉ አንድ ጊዜ መሞት ከዚያ በኋላ ፍርድ ተወስኖባቸዋል ይላል(ዕብ. 9፡27፣1ቆሮ.15፡22) ስለዚህ ሰዎች ከሙታን ተነስተዉ አዲስ ህይወትን ለመኖር ፍርድንም ለመቀበል የሚያገኙት ከሞት መነሳት የሙታን ተንሳኤ ይባላል ፡፡
• Anastasis (ግሪክ) Gk. (Ana= up stasis= stand = stand up)
• ትንሳኤ (geez)
15.2. ትንሳኤ ሙታን አለ
• ትንሳኤ ሙታን ባይኖር ሌሎች ስብከቶች ሁሉ ከንቱ ይሆኑ ነበር (1ቆሮ. 15፡12-19) ፡፡ ‹‹ትንሳኤ ሙታን›› መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ያለዉ አስተምህሮ ነው ፡፡ ‹‹ሙታን ህያዋን ይሆናሉ በድናቸዉም ይነሳል ›› (ኢሳ.26፡19) ፡፡ ‹‹ከምድር አፈር ዉስጥ ካንቀላፉት ብዙዎች ይነቃሉ፡፡
• አንዳንዶቹ ለዘላለም ህይወት ሌሎችም ለዉርደትና ለዘላለም ጉስቁልና ይነሳሉ›› (ዳን. 12፡2) ፡፡
• ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በስጋዉ ወራት በምድር በተመላለሰባቸዉ ዓመታት ‹‹የሙታን ተንሳኤ የለም›› የሚሉ ሳዱቃዊያን ነበሩ፡፡ በመጀመሪያዋ ቤ/ክ ዘመንም ቢሆን ‹‹የሙታን ትንሳኤ የለም›› የሚሉና የሚያስተምሩም ነበሩ (ማቴ.22፡29-32፣ማር.12፡24-27፣ሉቃ. 20፡34-38፣ ዮሐ.5፡25- 29፣6፡39-54፣ 11፡24-25፣ የሐዋ.2፡24- 32፣ 13፡32-37) ፡፡
• ‹‹ክርስቶስ ከሙታን እንደተነሳ የሚሰብክ ከሆነ ግን ከእናንተ አንዳንዶቹ፡- ትንሳኤ ሙታን የለም እንዴት ይላሉ? (1ቆሮ.15፡12-19)
15.3. ሙታን እንዴት ይነሳሉ? (1ቆሮ. 15፡35-50)
• በአካለ ስጋ የሞቱ ሁሉ ድንገት ሰው ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ይነቃሉ (ይነሳሉ)፡፡ የሚነሳው ስጋዊ አካል ምን ዓይነት ይሆናል ለሚለው ከቅድመ ሞት በፊት ከነበረው አካል ፈጽሞ የተለየ ነው፡፡
15.4. የሙታን ትንሳኤ ቅደም ተከተል (1ቆሮ. 15፡23)
• የሙታን ሁሉ ትንሳኤ በአንድ ጊዜ አይሆንም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በቅደም ተከተል የሚከናወኑ የተለያዩ ትንሳኤዎች ስለመኖራቸዉ በግልጽ ያስረዳል፡፡ እነርሱም፡-
15.4.1. የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤ
• ለዓለም ሁሉ ኃጢአት ቤዛ በመሆን በእንጨት ተሰቅሎ በመሞት የተቀበረዉና መጽሐፍም እንደሚል በሶስተኛዉ ቀን የተነሳዉ እርሱ የመጀመሪያና በኩር ነዉ ፡፡ ‹‹አሁን ክርስቶስ ላንቀላፉት ሁሉ በኩራት ሆኖ በእርግጥ ከሙታን ተነስቷል›› (1ቆሮ. 15፡20፣23) ፡፡
• ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤ በፊት በነቢያት በራሱም በክርስቶስ ኢየሱስ አገልግሎትና እንዲሁም በሐዋርያት አገልግሎት ሙታን ተነስተዋል፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ ከሞት የተነሱቱ ሁሉ ተመልሰዉ ሞተዋል፡፡
የእርሱ ትንሳኤ ግን ፡-
• የሞትን ጣር አጥፍቶ ዳግመኛ ላይሞትና ከዘላለም እስከ ዘላለም ህያዉ ሆኖ ይኖራል (ራዕ.1፡18) ፡፡
• በሁሉ ነገር ላይ የበላይነቱን ያሳየበት ትንሳኤ ነዉ (ቆላ.1፡18) ፡፡
እርሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን በመነሳቱ የተገኙ ዉጤቶች ምንድን ናቸዉ?
ሀ. ለአማኞች ሁሉ ከሞት መነሳት የታመነ ተስፋ ነዉ (1ቆሮ.15፡23)
ለ. ሞት ከእንግዲህ እርሱን ላይገዛዉ ሞትን ድል ነስቶታል (ሮሜ. 6፡8-10)
ሐ. የሞትና የሲኦል መክፈቻ በእጁ ሆኗል (ራዕ. 1፡18)
መ. በሞት ላይ ስልጣን ያለዉን ዲያቢሎስን ሽሮታል (ዕብ. 2፡14)
ሠ. እኛ ዳግመኛ ተወልደን ለህያዉ ተስፋ በቅተናል (1ጴጥ. 1፡3-5)
15.4.2. የቅዱሳን ትንሳኤ
ይህኛዉ ትንሳኤ የትንሳኤ በኩር ከሆነዉ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤ በመቀጠል ሐዋርያዉ ጳዉሎስ ‹‹የክርስቶስ የሆኑት›› በማለት የገለጻቸዉ የሚነሱበት ትንሳኤ ነዉ (1ቆሮ.15፡23) ፡፡
በዚህኛዉ ትንሳኤ ጌታችን ኢየሱስ ቤተክርስቲያንን ለመዉሰድ ሲመለስ በእርሱ አምነዉ የሞቱት ቅዱሳን አስቀድመዉ ይነሳሉ፣ በህይወት ያሉት ደግሞ ስጋቸዉ በክብር ተለዉጦ በአንድነት ጌታን በአየር ላይ ለመቀበል በደመና ይነጠቃሉ (1ቆሮ. 15፡51-53፣ 1ተሰ. 4፡13-18) ፡፡
ሀ. የቅዱሳን ትንሳኤ
– የጻድቃን ትንሳኤ (ሉቃ.14፡14)
– የህይወት ትንሳኤ (ዮሐ.5፡29)
– የትንሳኤ ልጆች እና የእግዚአብሔር ልጆች (ሉቃ.20፡36) ትንሳኤ ተብሎ ተጠርቷል፡፡
ይህ የቅዱሳን ትንሳኤ በመቀጠል ከሚሆነዉ ከኃጢአን ትንሳኤ አንጻር የፊተኛዉ ትንሳኤ ተብሏል (ራዕ.20፡1-6) ፡፡
ለ. የቅዱሳን ትንሳኤ ዓላማ
የቅዱሳን ትንሳኤ፡
1. ክቡር የሆነዉን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ስጋ እንዲመስል፣ የሚሞተዉና የሚበሰብሰዉ ስጋችን ተለዉጦና ሞት ዳግመኛ የማይገዛዉን የትንሳኤን አካል ለብሰን ወደሰማይ አገራችን ለመሄድ ብቁ ያደርገናል(1ቆሮ.15፡51-54፣ ፊል.3፡21፣ ዮሐ.14፡1-3) ፡፡
2. ቅዱሳን በምድር ህይወታቸዉ በመንግስቱ ዉስጥ ላበረከቱት አስተዋጽኦና ለደከሙበት ስራ ከጌታ ዘንድ ዋጋንና ሽልማትን ይቀበላሉ (ሉቃ. 14፡14፣ 1ቀሮ. 3፡14 ራዕ. 22፡12-15፣17፣20)
በታማኝነት ሲያገለግሉት የቆዩትንና የሚቆዩትን በዚያን ጊዜ ብድራታቸዉን (rewards) ጌታ ይከፍላቸዋል (ሉቃ. 12፡35-48 ፣ 2ጢሞ.4፡6-8 ‹‹ያን ቀን››) ፡፡
2. ጌታ በቅዱሳን ጠላት ላይ ሊበቀልና ለቅዱሳኑ በጽድቅ ሊፈርድ የቅዱሳን ትንሳኤን አዘጋጀ (1.ቆሮ.15፡54-58፣ኢሳ. 63፡4) ፡፡ “For the day of vengeance is in my heart, and the year of my redeemed has come” (መዝ.50፡1-6፣ራዕ.6፡9-17፣14፡14- 20፣ ማቴ.13፡30፣ ማቴ.24፡29-31 ሉቃ.17፡22-37 2ተሰ.1፡7-10) ፡፡
4. የቤተክርስቲያን ሰርግና የበጉ ሰርግ እራት ይሆናል (ራዕ. 19፡7-9) ፡፡
5. ከታላቁ መከራ ዘመን ቁጣ ቅዱሳን ይድናሉ (ራዕ. 3፡10 (ራዕ. 6-19) ፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ስለመጨረሻዉ ዘመን ሲያስተምር ስለታላቁ መከራ እንዲህ በማለት ገልጾታል፡፡
‹‹በዚያን ጊዜ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ሆኖ የማያዉቅ ከዚያም በኋላ የሚስተካከለዉ የሌለ ታላቅ መከራ ይሆናል›› (ማቴ. 24፡21) ፡፡ ታላቁ መከራ የተባለበትም ከአሁን በፊት ሆኖ የማያዉቅ ታላቅ የመከራ ጊዜ ስለሚሆን ነዉ (ዳን. 12፡1) ፡፡
የታላቁ መከራ ዘመን ለ7 ዓመት እንደሚሆን መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል፡፡ ቅዱሳን (ቤተክርስቲያን) ይህ የ7 ዓመቱ ታላቅ መከራ ዉስጥ ያልፋሉ? ወይስ አያልፉም? ለሚለዉ ጥያቄ የተለያዩ አመለካከቶች ወይም አቋሞች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ እነዚህም፡- ቅድመ ፣ አጋማሽ እና ድህረ መከራ አመለካከቶች ናቸዉ፡፡ ይሁን እንጂ ከሚከተሉት ምክንያቶች (መጽሐፍ ቅዱሳዊ) በመነሳት
ቤተክርስቲያን በሰባቱ ዓመታት የመከራ ጊዜ ዉስጥ አታልፍም ብለን ማመን እንችላለን፤
ሀ. ታላቁ መከራ ከተጠቀሰበት የራዕይ መጽሐፍ (ከምዕ.5 እስከ ምዕ. 19 ድረስ) የቤ/ክ ስም አንድም ቦታ ተጠቅሶ አናገኝም፡፡ ከምዕ.1 – 4፡20 ብቻ ቤ/ክ ተጠቅሳለች ፡፡
ለ. ለቤተክርስቲያን የመዳን ተስፋ ተሰጥቷታል (ራዕ. 3፡10) እንጂ የመከራና የቁጣ ቀጠሮ አልተሰጣትም (ዮሐ. 3፡36፣1ተሰ.5፡9፣ ዮሐ. 14፡1-3) ፡፡
ሐ. ከእግዚአብሔር ባህሪይ እንደምንረዳዉም ፍርድ ከመገለጹ በፊት አስቀድሞ ጌታ ኢየሱስ ልጆቹን ያወጣቸዉ ነበር ፤ ሎጥ (ዘፍ. 19፡22) ፣ ኖህም ቢሆን ከጥፋት ዉኃ በፊት (ዘፍ.7፡1-4)፣(ራዕ. 4፡1፣ 11፡12- 14) ፡፡
6. ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግመኛ ተመልሶ ለሺህ ዓመት በምድር ላይ ይነግሳል፡፡ እርሱ ለሺህ ዓመት መንግስቱን በዚህ ምድር ላይ መስርቶ ሲነግስ ከእርሱ ጋር ቅዱሳን ለሺህ ዓመት በምድር ላይ አብረው ይነግሳሉ (ራዕ. 20፡1-10 (4-5) ፡፡
• በሺህ ዓመት መንግስት
ሀ. ሰይጣን ተይዞ ለሺህ ዓመት ይታሰራል፡፡
ለ. ቅዱሳን (የብ/ኪ እና የታላቁ መከራ ቅዱሳን) ከክርስቶስ ጋር 1000 ዓመት በምድር ላይ ይነግሳሉ (ሚኪ. 4፡1-2 ኢሳ፡2፡1-4) ፡፡
• የሺህ ዓመት መንግስት ባህሪያት
1. እርግማን ከምድር ላይ ሙሉ በሙሉ ይነሳል፡፡
• ምድር ሁሉ ፍሬያማ ትሆናለች (ኢሳ. 35፡1-2 ) ፡፡
2. ፍጹም ሰላም በምድር ላይ ይሆናል፡፡
• የሰላሙ አለቃ የሚገዛበት ፣ ጠላት ዲያብሎስ የሌለበት ጦርና፣ የጦር ወሬ የማይሰማበት፣ ይልቁንም የጦር መሳሪያዎች የልማት መሳሪያዎች ሆነዉ የሚለወጡበት ይሆናል (ሚኪ. 4፡1-3፣ኢሳ.2፡1-4፣9፡7፣ዘካ. 9፡10) ፡፡
• በእንስሳት መካከል እንኳን ፍጹም ሰላም ይሰፍናል (ኢሳ.11፡6-9፣65፡25)፡፡
• ፍጥረት ከጥፋት ባርነት ነጻ ይወጣል (ሮሜ. 8፡19-22) ፡፡
3. የሰዉ እድሜ በምድር እጅግ ይረዝማል (ኢሳ. 65፡22) ፡፡
4. አይሁዶች ወደ እየሩሳሌም ይሰበሰባሉ፤
• የመንግስቱ ማዕከል በዚህ በኢየሩሳሌም ከተማ ይሆናል፡፡
• መቅደሱ እንደገና ይገነባል (የፈረሰዉ የዳዊት ድንኳን እንደገና ይሰራል)
(ሚኪ.4፡8 አሞ. 3፡11-12) ፡፡
15.4.3. የኃጥአን ትንሳኤ
በመጨረሻም ክርስቶስን ሳይለብሱ ያልዳኑና ስማቸዉ በህይወት መዝገብ ዉስጥ ተጽፎ ያልተገኘ ሁሉ ለፍርድ ይነሳሉ (ራዕ. 20፡5) ፡፡ ይህ የመጨረሻዉ የኃጢአን ትንሳኤ የሚሆነዉ ከሺህ አመት መንግስት በኋላ የሚሆን ነዉ (ራዕ. 20፡5፣11-15) ፡፡
ሀ. የኃጥአን ትንሳኤ ዓላማ ፡-
1. በስሙ በመጠመቅ የኃጢአትን ስርየት ባለማግኘታቸዉ የኃጢአትና የስራቸዉን ደመወዝ የሆነዉን የዘላለም ሞትን ይቀበላሉ (ሮሜ. 6፡23)
2. ለዘላለም ከእግዚአብሔር ተለይተዉ የዘላለም የገሃነም እሳት ፍርድን ተቀብለዉ ለሰይጣንና ለወደቁት መላዕክት ወደተዘጋጀዉ ስፍራ ለዘላለም ወደሚሰቃዩበት፣ እሳቱ ወደማይጠፋበትና ትሉ ወደማይሞትበት ወደ ዘላለም ጉስቁልና አልፈዉ ይሰጣሉ (ማቴ. 25፡41-46፣ራዕ.20፡11-15) ፡፡
መንፈሳዊ ስጦታዎችና ተፈጥሯዊ ችሎታዎች
ግንኙነታቸው
1ኛ. የሁለቱም ምንጭ እግዚአብሔር መሆኑ፣ እግዚአብሔር በተፈጥሮአችን ውስጥ ለተቀመጡ ልዩ ልዩ ችሎታዎቻችን ምንጭ ነው፡፡ ማንም ለራሱ ያንን ማድረግ አይቻለውም፡፡ ተፈጥሮአዊ ችሎታዎቻችን በስልጠና ቢዳብሩም በምርጫችን የኛ ልናደርጋቸው አንችልም፡፡ ድምጻችንን፣ በባሕሪያችን ውስጥ የተቀመጡ ልዩ ልዩ የማንነቶቻችን መግለጫዎች የመነጩት ከሰጪው ነው፡፡
2ኛ. ተፈጥሮአዊ ችሎታዎች ለበጎ ምግባር የሚውሉ መሆናቸው፣ በተፈጥሮ ችሎታችን ውስጥ የተቀመጡ አንዳንድ ተሰጥኦዎች እግዚአብሔር በአማኙ ውስጥ ለሚሠራው ሥራ አመቺ ሁኔታን ይፈጥራሉ፡፡ ለምሳሌ ድምጻቸው መረዋ የሆኑ ሰዎች ዘፋኝ ሆነው ያገለገሉትን ያህል ዘማሪ ሆነው ሊያገልገሉ የሚችሉበት ሁኔታ መፈጠሩ፣ በባህሪያቸው ለጋስ የሆኑ ሰዎች የምህረት አድራጊነት ጸጋ በውስጣቸው ሊሠራ መቻሉ፣ ተናጋሪና ፀሐፊ የሆኑ ሰዎችን ሰባኪና መምህራን ለመሆን መቻላቸው ከብዙ በጥቂቱ ይጠቀሳሉ፡፡
መንፈሳዊ ስጦታዎች
የጸጋ ስጦታዎች ስማቸው እንደሚያመለክተው እግዚአብሔር ከርህራሄው የተነሳ ቅጣት ለሚገባቸው ሰዎች ያደረገው ልግስናዎች ናቸው፡፡ ሁሉም አማኞች የዚህ እድል ፈንታ ተካፋይ ናቸው፡፡
ይሁን እንጂ ስጦታውን የሚቀበሉና በአግባቡ የሚያስተናግዱ ብዙ አይደሉም፡፡ መንፈሳዊ ስጦታዎች ለተቀባዩ ጥቅምና መታነጽ የተሰጡ ቢሆንም አውራ ግባቸው የክርስቶስን አካል ማነቃቃትና መገንባት ነው፡፡ ስለ ስጦታ በተጠቀሰባቸው አራቱ የአዲስ ኪዳን ክፍሎች ወደ ሃያ የሚሆኑ ስጦታዎች ተዘርዝረው እንመለከታለን፡፡
ስጦታን እንዴት ማወቅ ይቻላል
እግዚአብሔር ስጦታ ሰጥቶኛል? ስጦታዬስ ምንድነው? የተፈጥሮ ችሎታዬን የእግዚአብሔር ስጦታ ነው ማለት እችላለሁ? ስጦታ ያድጋል አያድግም? … ሌሎች ሌሎች ጥያቄዎች ይኖሩን ይሆናል። ረጋ ብለን እያስተዋልን እግዚአብሔር መልስ ይሰጣል።
እያንዳንዱ ክርስቲያን አንድ ወይም ከዚያ የበለጠ ስጦታ አለው
በጌታ ኢየሱስ ስም ተጠምቀው ዳግም የተወለዱ፣ በክርስቶስ ደም በተዋጀው ቤተሰብ ውስጥ እያንዳንዱ በእግዚአብሔር ቃል የተወለደ ልጅ ስጦታ ተቀብሏል። “ልዩ ልዩን የእግዚአብሔርን ጸጋ ደጋግ መጋቢዎች እንደ መሆናችሁ እያንዳንዳችሁ እያሳስበናል (1ኛጴጥ. 410)። እያንዳንዱ ክርስቲያን ስጦታውን የማወቅና የማሳደግ ኃላፊነት አለበት። ልክ እንደ ዘር ወይም አዲስ እንደ ተወለደ ሕጻን መንፈሳዊ ስጦታዎችም ከትንሹ ይጀምሩና በጥንቃቄ ከተያዙ ያድጋሉ። በፍቅርና በእግዚአብሔር መንፈስ በመመካት ሳናቋርጥ ከተጠቀምንባቸው ግባቸውን የሚመቱ ጠንካራ መሣሪያዎች ይሆናሉ። ስጦታውን ባሳደገ መጠን የእግዚአብሔር ባሪያ ራሱ ጠቃሚ ሰው መሆን ይጀምራል። ስጦታው ከተቀባዩ አኳኋን፣ ባሕርይና ካለፈበት ልምምድ ጋር ይስማማል። ስጦታው የወደ ፊት ኑሮውን እንኳ ሊወስን ይችላል። ምክንያቱም ስጦታዎቹ የእግዚአብሔር መንፈስ እያንዳንዱ ክርስቲያን በሕይወት ዘመኑ ሊፈጽማቸው የሚገባቸውን ሥራዎች የሚያሳዩ ጠቋሚዎች ስለሆኑ ነው። ስጦታ ላንተ በግልህ የሚያስደስትህና ስሜት የሚያሳድርብህ የራስህ ስጦታ ምን ምን መሆኑን ለይተህ ስታውቅ ነው። ስጦታህን ለማወቅ ከሚረዱህ ነገሮች አራት ያህል እንጠቅሳለን።
በተፈጥሮ ችሎታህ ጀምር፣ በዚያ ግን አትቁም
የተፈጥሮ ችሎታና መንፈሳዊ ስጦታ አንድ ባይሆኑም እንኳ የተያያዙ ነገሮች ናቸው። እንድ ሰው እንዳለው ስጦታዎቹ “… በውስጥ የተደበቀ የተፈጥሮ ችሎታን ይጠቁማሉ”። እንግዲህ ስጦታን ለማወቅ ከሚደረጉ የመጀመሪያ እርምጃዎች አንዱ የተፈጥሮ ችሎታን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ መጠቀም መጀመር ነው። እንግዲህ የመንፈሳዊ ስጦታን አንድ መለኪያ በጸሎት ማወቅ ይቻላል ። በእምነት ላይ በተመሠረተ ጽኑ ጸሎት አንጻር ማየት እንችላለን። ይኸም ጸሎት እግዚአብሔር የሚያስፈልገንን እንዲሰጠን አንዴ ጠይቀነው የጠየቅነውን ነገር ለማግኘት በትዕግስት የምንጠባበቅበት ጸሎት መሆኑን የእግዚአብሔር ቃል ይናገራል።
የተፈጥሮ ችሎታን በሥራ ላይ ስናውል በውጤቱ አንድ ከተፈጥሮ ውጪ (መንፈሳዊ) የሆነ ለውጥ በሰው ላይ መምጣቱ ነው። ይህም ማለት ሰዎች ወደ ጌታ ኢየሱስ ሲሳቡ ወይም በእምነታቸው ሲታነጹ ነው። ይህ መታነጽ ያለ መንፈስ ቅዱስ አይመጣም። ሆኖም አንድ ሰው የተፈጥሮ ችሎታ ኖሮት ከዚህ ጋር የተያያዘ መንፈሳዊ ስጦታ ላይኖረው ይችላል። ለምሳሌ ስድስት ዘማሪዎች ሁሉም በሙዚቃ ችሎታቸው እኩል የሆኑ በተለያዩ ጊዜአት ይዘምራሉ። አድማጮችም በሰሙት ሙዚቃ በጣም እንደ ተደሰቱ በማድነቅ ይናገራሉ። ነገር ግን ከስድስቱ አንዱ ከተፈጥሮ ችሎታው ጋር መንፈሳዊ ስጦታም አለው። እሱ ሲዘምር የእግዚአብሔር ህልውና በአዲስ መንገድ ይከሰታል። ሰዎች ወደ ጌታ ኢየሱስ ይጠጋሉ። የእግዚአብሔር መንፈስ በመዝሙሩ ቃላት ውስጥ ለሕይወታቸው የሚያስፈልገውን መልእክት ያስተላልፋል። ብቻ … አንድ መለኰታዊ ነገር ይፈጸማል። እኩል የተፈጥሮ ችሎታ ካላቸው ከሌሎቹ ከአምስቱ በተለየ ሁኔታ ያ አንድ ዘማሪ መንፈሳዊ ስጦታውን በሥራ ላይ እያዋለ ነው።
አንዳንድ መንፈሳዊ ስጦታዎች “ከተሰወሩ” የተፈጥሮ ችሎታዎች ጋር የተያያዙ ናቸው።
ቤተክርስቲያን የምትልህን አድምጥ
ሌሎች ከአዲስ አንጻር ያዩናል። እኛ ራሳችንን ከምናውቀው በተለየ መንገድ ያውቁናል። በግል መለኪያችን ብቻ ራሳችንን ከመዘንን ስለ ራሳችን የማናውቃቸውን ድብቅ ነገሮች ሳናስተውል እንቀራለን። የተቀበልነውን ስጦታ እንድናስተውል ሌሎች ሊረዱን ይችላሉ። ስጦታህን ለማወቅ እንዲረዱህ ባለህ ስጦታ መትጋት ጥሩ ነው። ጊዜ ወስዶ ከመጋቢና ከሌሎች አገልጋዮች ጋር መጸለይ መልካም ነው። ይህ አንዱ የሌላውን ስጦታ በመግለጽ እንዲተባበር ሊረዳ ይችላል። ይህ መንገድ ስለ እግዚአብሔር ስጦታዎች በቂ የሆነ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አመለካከት ሲኖርበት ግቡን ይመታል። የእግዚአብሔር ሕዝብ ኅብረት በሌላም መንገድ ሊጠቅመን ይችላል። የቤተ ክርስቲያን አባሎች ወይም መሪዎች አንዳንድ ኃላፊነቶችን እንድንቀበል ወይም የተለያዩ ሥራዎችን እንድንፈጽም ሊጠይቁን ይችላሉ። የወጣት መክሊት አገልግሎት ውስጥ እንድናገለግል ፣የሰንበት ትምህርት እንድናስተምር ከተጠየቅን ምናልባት የማስተማር ስጦታ ኖሮን ይሆናል። በቤተ ክርስቲያን ባሉ አገልግሎት ውስጥ ሥራ ቢሰጠን ከብዙ ስጦታዎች አንዱን ሊጠቁመን ይችላል፤ ማበረታታት፣ እርዳታን ማድረግ፣ አስተዳደርን ወይም ሌላ ስጦታን።
አንድ ሰው ያለ መንፈሳዊ ስጦታ የማስተማርን አገልግሎት ጀምሮ ይሆናል። ሌላው ደግሞ ያለ ስጦታው በኰሚቴ ውስጥ ሊያገለግል ይችላል። ግን ምንም ያህል የሚያበረክቱት ጠቃሚ ነገር አይኖርም። አገልግሎት ቢኖረንም መንፈሳዊ ስጦታ እለን ማለት ማረጋገጫ አይሆንም። ይህ የሚያሳየን ሥራውን እንድናደርግ ዕድል እንደ ተሰጠን ብቻ ነው። ክርስቲያን በተሰጠው አገልግሎት ውስጥ ምንም መንፈሳዊ ስጦታ ካላየበት የአገልግሎቱ ጊዜ እስኪያልቅ ጠብቆ ወደ ሌላ አገልግሎት ቢዛወር ይሻላል። ስጦታን ማሳደግ ብዙ ጥረትና መውደቅና መነሳት የሚጠይቅ ሥራ ነው። ነገር ግን ሰው ከሾመን ሹመት ይልቅ እግዚአብሔር የሰጠን አገልግሎት ይበልጣል። ስለዚህ ከላይ በቃሉ ላይ እንዳየነው ትሁት በመሆን ጸጋውን እንዲሰጠን መለመን አለብን፡፡
በመውደቅ በመነሳት ተማር
ስጦታህ በሌሎች ላይ ያመጣውን ለውጥ ለማስተዋል ሞክር። ምን እንደሚሰማቸው ለማወቅ ሞክር። እግዚአብሔር ያንን ችሎታ ሌሎችን ከመውደቃቸው ለማንሳት እየደጋገመ ከተጠቀመበት ምናልባት እሱ ስጦታህ ይሆናል።
ስታገለግል በሚሰጥህ እርካታ ስጦታህን ለማወቅ ሞክር
መንፈሳዊ ስጦታህን በቤተ ክርስቲያን ክልል ብቻ አትወስነው። እግዚአብሔር የሚሰጥህ ማንኛውም የሥራ ስሜት ለመንፈሳዊ ስጦታ ፍንጭ እንደሆኑ ለማየት ሞክር። ለምሳሌ አንድ ሰው በእጅ የሚሠራ ነገር ማድረግ ይወዳል። መኪና መጠገን፣ የተሰባበሩ ነገሮችን ማስተካከል…፤ ይህ ሰው ከዚህም ሌላ ከሰዎች ጋር መሥራት በጣም ይወዳል እንበል። ከተፈጥሮ ችሎታው ጋር የመርዳት ስጦታም አለው ማለት ነው (1ኛ ቆሮንቶስ 1228)። ከዚህ የተነሳ ሰዎች እንዲረዳቸው ሁልጊዜ ይጠሩታል። ይህም የመርዳት አገልግሎት ጌታ ኢየሱስን ከማስከበሩም ሌላ ይህንን ወንድም በጣም ያረካዋል። አስተውል፦ መንፈሳዊ ስጦታን መጠቀም ደስታንና እርካታን ያመጣል። እርግጥ አንዳንዶቹ ይህንን ደስታና እርካታ በሙላት ላያገኙ ይችላሉ ይህ የሚሆነው የእግዚአብሔርን መንፈስ ስለሚያሳዝኑ ነው። ስጦታ ከእግዚአብሔር ቢሰጥም ተቀባዩ ለራሱ ክብር ሲያደርገው ሊያበላሸው ይችላል። ነገር ግን የአካሉ ራስ ከሆነው ከክርስቶስ ጋር ትክክለኛ ግንኙነት ሲኖር የአካሉ ብልቶች ሁሉ በስጦታው ይደሰታሉ።
ስጦታችንን ለማወቅ በምናደርገው ጥረት የውድድር መንፈስ ጨርሶ መወገድ አለበት። ከሌሎች ጋር ራሳችንን ማስተያየትም ሆነ ማወዳደር ፍጹም አልተፈቀደም። ይህን ማድረግ ሁሉም ቻይና ሁሉን አዋቂ የሆነውንና ስጦታውንም የሚሰጠውን እግዚአብሔርን አለማክበር ነው። ከዚህ ይልቅ ሌሎች ስጦታቸውን እንዲለዩ ያንተንም እንዲያሳዩህ እርዳቸው። በስጦታቸው መደሰትንና መጠቀምን ተማር። ስለነርሱ እግዚአብሔርን አመስግን። በሌሎች ስጦታ መደሰት ስለ ሌሎች ያለንን መጥፎ አስተያየት ለማስወገድ የክርስቶስን አካል አንድነት ለመጠበቅና ለመረዳዳት ይጠቅማል። መንፈሳዊ ስጦታዎች በፍቅር ካልተሠራባቸው ምንም አይጠቅሙም (1ኛ ቆሮንቶስ 13)። ፍቅር የጐደለውን ይሞላል። ያለመረዳትንና ውድቀትን ያስወግዳል። ፍቅር ይቅርታ ያደርጋል፤ ያማክራል፤ ያስተካክላል። ፍቅር የመንፈስ ስጦታዎችን ማሰናከያዎች ሳይሆኑ ማስተካከያዎች ያደርጋቸዋል። ደስ የሚልና ጠቃሚ ሕይወት እንዲኖርህ መንፈሳዊ ስጦታዎችህን እወቅ። በክርስቶስ አካል ውስጥ ያለህን የአገልግሎት ድርሻ አሳድግ። ለሌሎች መታነጽ ስጦታህን በፍቅር ለመጠቀም በሙሉ ኃይልህ ሥራ። “ልዩ ልዩ የእግዚአብሔርን ጸጋ ደጋግ መጋቢዎች እንደ መሆናችሁ እያንዳንዳችሁ የጸጋን ስጦታ እንደ ተቀበላችሁ መጠን በዚያው ጸጋ እርስ በርሳችሁ አገልግሉ።”
እምነት /FAITH IN GOD/
በክርስትና ሕይወታችን ስኬታማ ለመሆንም እምነት ያስፈልገናል፣ የጻድቅ መኖሪያዉ እምነት ነዉና (ሮሜ1፡17) ፡፡ያለእምነትም የሆነ ነገር ሁሉ ኃጢያት ነዉ (ሮሜ.14፡23) ፡፡
8.1. እምነት ያልሆኑ ነገሮች
እምነት ስንል የሚከተሉትን ማለታችን አይደለም ፡፡
ሀ. እምነት ኃይማኖት (Religion) አይደለም ፡፡ ብዙ ጊዜ ሰዎች ‹‹እኛ የራሳችን እምነት አለን ››ሲሉ ይደመጣሉ ፡፡
ለ. እምነት ከአእምሮ ጋር መስማማት አይደለም ፡፡እምነት በአእምሮ ስሜት ላይ የሚደገፍ የአእምሮ ቀመር አይደለም ፡፡ ብዙ ክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል እንደሆነና እዉነትም እንደሆነ፣ እንደሚያምኑም ይናገራሉ ፡፡ ነገር ግን ይህ አይነቱ እምነት ህይወታቸዉንና ኑሮአቸዉን የማይቀይር ነዉ (ያዕ 2፡14) ፡፡ ይህ አይነቱ እምነት አጋንንትም ያላቸዉ የእምነት አይነት ነዉ (ያዕ.2፡19)
ሐ. እምነት እግዚአብሔርን እንደፈለግን የምናንቀሳቅስበት እና በግላዊ ምቾታችን ላይ የተደገፈ አይደለም፡፡
መ. እምነት ተስፋም፣ መልካም መሻትም አይደለም፡፡ ተስፋ መልካም ነዉ፡፡ በትእግስትም የወደፊቱን መጠበቅ ያስችለናል ፡፡ ይሁን እንጂ እምነት ተስፋን አሁን እንዳገኘ ይቀበላል፡፡
ተስፋ የአእምሮ (የነፍስ) ሲሆን (1ተሰ.5፡8፣ ዕብ.6፡19) የነፍስ መልህቅ ነዉ፡፡ ተስፋ ልናምን በምንችልበት ስፍራ ላይ አጽንቶ ያቆመናል እንጂ ግን ያለ ተስፋ እምነት የለም፡፡
በእግዚአብሔር እምነት ሁልጊዜ በልብ ነዉ (ሮሜ. 10፡10) ፡፡
8.2. እምነት ምንድን ነዉ?
መጽሐፍ ቅዱስ እምነትን በዕብ. 11፡1 እንደሚተረጉመዉ፡-
ሀ. እምነት ማለት እግዚአብሔር የተናገረዉን ተስፋ ሁሉ እንደፈጸመዉ እርግጠኛ ሆኖ መረዳት ነዉ (The dictionary describes faith as a complete trust and confidence, firm belief without
logical proof) ፡፡
ለ. እምነት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሰማያዊ ስፍራ በመንፈሳዊ በረከት ሁሉ የባረከንን መቀበል መቻል ነዉ (ኤፌ.1፡3) ፡፡
ሐ. እምነት ተስፋዎቻችን ሁሉ እንደተቀበልን የሚያረጋግጥ በእጃችን (በልባችን) ያለ ቼክ ነዉ፡፡ (1ዩሐ. 5፡14-15፣ ማር.11፡23-24) ፡፡
መ. እምነት እግዚአብሔር የተናገራቸዉ ቃሎች ላይ ተመስርቶ የሌለዉን ማለትም በስጋ አይን ያላየነዉን እንዳለ አድርጎ መጥራት መቻል ነዉ፡፡ ይህም ማለት ነገሮች በእግዚአብሔር እንደሆኑ ማየት እንጂ በተፈጥሮ እይታ አንጻር የሚመስሉትን ማየት አይደለም (ሮሜ.4፡16-17) ፡፡ እግዚአብሔር በዘፍ.17፡5 ላይ ሲናገር የአሕዛብ አባት አደርግሃለሁ ሳይሆን አድርጌሃለሁ በማለት ነዉ፡፡ስለዚህ የእምነት አባት የሆነዉ አብርሃም በሚያደርገዉ ሁሉ በእግዚአብሔር እምነት ነበረዉ፡፡
• በአለማመን አልተጠራጠረም ፡፡
• ተስፋ የሰጠዉ እግዚአብሔር የታመነ እንደሆነ ቆጠረ ፡፡
• በእግዚአብሔር ቃል ላይ የሚቃረንን ማንኛዉንም የተፈጥሮ መረጃዎችን አልተቀበለም (ዕብ.11፡8-12፣ሮሜ. 4=16-22) ፡፡
8.3. እምነትን እንዴት እናገኛለን?
ያለ እምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት እንደማንችል የተናገረዉ እርሱ እምነትንም ማግኘት የምንችልበትንም መንገድ ነግሮናል፡፡ እምነት የሌለን ከሆንን ተጠያቂ ልናደርገዉ የምንችለዉ የራሳችንን አለማወቅ እንጂ እግዚአብሔርን ሊሆን አይችለም ፡፡
እምነት የእግዚአብሔርን ቃል በመስማት ይመጣል (ሮሜ.10፡17) ፡፡ ከዚህ አንጻር እምነት የእግዚአብሔር ስጦታ እንደሆነ እንመለከታለን ፡፡ ‹‹ፀጋዉ በእምነት አድኗቸዋልና ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነዉ እንጂ ከእናንተ አይደለም ማንም እንዳይመካ ከስራ አይደለም (ኤፌ.2፡8) ፡፡
የእግዚአበሔር ቃል በራሱ የእምነት ቃል እንደሆነ መጽሐፍ ይናገራል፡፡ እምነትም የሚገኘዉ ይህንኑ የእምነት ቃል ከመስማት ነዉ (ሮሜ. 10=8፣14፣17) ፡፡
• ቆርነሊዎስና ቤተሰቡ መዳንን ለማግኘት የሚያስችላቸዉን እምነት በመስማት አገኙ (ዮሐ.10፡5-6፣ 11፡13)፡፡
• በልስጥራንም እግሩ የሰለለዉ ሰዉ ጳዉሎስ የእግዚአብሔርን ቃል ሲናገር ሰምቶ እንዳመነና እንደተፈወሰ (የሐ.14፡8-10)፡፡
• ከ12 ዓመትም ጀምሮ ደም የሚፈሳት ሴት የኢየሱስን ወሬ ሰምታ ተፈዉሳለች (ማር.5፡25-34)፡፡
• የእግዚአብሔርን ቃል ዘወትር ሰምተን በልባችን እንድንጠብቀዉና የሚጠቅመን እንዲሆን የእግዚአብሔር ቃል ያሳሰበናል (ምሳ.4፡20-22) ፡፡
8.4. እምነትን ማሳደግ
እምነት ልክና መጠን አለዉ (ሮሜ.12፡3-6)
• እምነት በስናፍጭ ቅንጣት ተመጥኗል
• እምነት ያድጋልም ‹‹ስለ እምነታችሁ ማነስ ነዉ›› ይላልና፡፡
እምነትን ልናሳድግበት የምንችልባቸዉን መንገዶች እንደሚከተለዉ ልናይ እንችላለን፡-
ሀ. ዘወትር የእግዚአብሔርን ቃል ማንበብ፣ መማርና መስማት (ምሳ. 4፡20-22) ፡፡
ለ. ዘወትር በመንፈስ ቅዱስ መሞላትና በመንፈስ ቅዱስም መጸለይ (ይሁዳ 20፣1ቆሮ.14፡4) የመንፈስ ፍሬ ተብለዉ ከተጠቀሱት ዉስጥ አንዱ እምነት ነዉ፡፡
ሐ. ዘወትር በምንሰማዉ የእግዚአብሔር ቃል መሰረት ተግባራዊ ርምጃዎችን በየደረጃዉ መዉሰድን መለማመድ፡፡ እግዚአብሔር በገለጠልን በጥቂቷ ነገር ታማኝ በመሆን ካልተገበርነዉ የበለጠዉን ነገር እግዚአብሔር አይገለጥልንም ፡፡
መ. የኑሮአቸዉን ፍሬ በመመልከት በእምነታቸዉ መምሰል ይቻል ዘንድ በተቻለ መጠን ሁሉ ከእምነት ሰዎች ጋር ጊዜን ማሳለፍ (ዕብ.13፡7፣ ምሳ.13፡20) ፡፡
ሠ. የእግዚአብሔር ቃል እንደሚያስተምረን እምነት የሚሰራዉ በፍቅር ነዉ (ገላ.5፡6) ፡፡ ለምሳሌ ያህል የመቶ አለቃዉ (ማቴ.8፡5-13) እና ከነናዊቷ ሴት (ማቴ.15፡21-28) ወደ ኢየሱስ እንዲቀርቡ ያነሳሳቸዉ ጉዳይ ፍቅር ነበር ፡፡ ሁለቱም ታላቅ እምነት የነበራቸዉ እንደነበሩ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አስረድቷል፡፡
ረ. የእምነት ምስክርነትን (confession) መጠበቅ (ዕብ. 10፡23፣ ሮሜ.10፡10፣ ኢያ.1፡8) ፡፡
ሰ. ዘወትር ቅድስናን መፈለግ (ዕብ.12፡14) ፡፡ የልብ ንጽህናና የይቅርታ ልብ ከሌለ የልብ እምነት እንዳይኖር አስተዋጾ ስላለዉ ነው፡፡
8.5. የእምነት ገጽታዎች
የዕብራዊያን መልእክት ምእራፍ 11‹‹የእምነት ምእራፍ›› በመባል ይታወቃል ፡፡ በምእራፍ ዉስጥ ሁለት የእምነት ገጽታዎች ተገልጸዋል፡፡ እነርሱም፡-
ሀ. የአሸናፊ ድል የመንሳት እምነት (victorious-overcomers) (1-35)
• ዳንኤል ከአንበሶች ጉድጓድ (ዳን.6)
• ሲድራቅ፣ ሚሳቅ እና አብድናጎ ከእቶኑ እሳት (ዳን.3)
• የባልቴቷ ልጅ ከሞት መነሳት (1ነገ.17)
• ዳዊት ከሰይፍ በተደጋጋሚ መዳኑ
ለ. በመከራ ጸንቶ የመታመን እምነት (faithfulness in suffering) (35-40)
• ኤርሚያስ በወህኒ (ኤር.37-38) ፤
• ኢሳያስ በመጋዝ ለሁለት ተሰንጥቆ ፤
• ሚኪያስ በጥፊ ሲመታ ፤
• ዘካርያስ እስከሞት በድንጋይ መወገር (2ዜና 24፣ማቴ23፡35-37) ፡፡
ስለዚህ እምነት ከመከራ ነጻነትን መቀበል፣ ከህመም መፈወስን እንዲሁም ለፍላጎታችን ሁሉ አቅራቦትን መቀበል ማለት ብቻ አይደለም ፡፡ እምነት እስራት በጸና ጊዜ፣ ጸሎታችን ተሰምቶ መልስ ያላገኘን በመሰለን ጊዜና ታእምራዊ አቅራቦቶችን ባላገኘን ጊዜም በመከራ ጸንቶ እግዚአብሔርን መታመን ነዉ፡፡ የቀደሙት የእምነት አባቶችም በምሳሌነታቸዉ የተመሰከረላቸዉ በነዚሁ በሁለቱም የእምነት ገጽታዎች ነበር (ዕብ. 11፡32-40) ፡፡
8.6. እምነት በአማኞች ህይወት እንዴት ሊገለጥ ይችላል?
እምነት በእግዚአብሔር ባህሪይ፣ ኃይልና በቃሉ ላይ የጸና መታመንን ይዞ አካሄዳችንን (ድርጊቶቻችንን) ከእርሱ ጋር በማድረግ ነዉ፡፡ ከዚህ አንጻር እምነት የሚገለጥባቸዉ መንገዶች የሚከተሉት ናቸዉ፡፡
• በአፍ ምስክርነት (statement of faith) (ሮሜ. 1፡5፣ ያዕ.2 14-26)
• በእምነት በመመላለስና በመኖር (2ቆሮ. 5፡7፣ ሮሜ.1፡17፣ገላ.2፡20)
8.7. የእምነት አስፈላጊነት
እግዚአብሔርን ማመን ወይም በእግዚአብሔር እምነት ለምን ያስፈልገናል?
ሀ. ያለእምነት መዳን አይቻልም (ዩሐ.3፡36፣ ኤፌ.2፡8) ፡፡ እምነት የፈዉስ፣ የአርነት አገልግሎትም ቁልፍ ነገር ነዉ፡፡
ለ. ዕብ.11፡6 እንደሚለዉ ‹‹ያለእምነትም ደስ ማሰኘት አይቻልም፤›› እኛ ደግሞ የተፈጠርነዉ ለእርሱ ደስታ ነዉ (ራዕ.4፡11፣ መዝ.147፡11) ፡፡ እርሱን ደግሞ ደስ የማናሰኝ ከሆንን የተፈጠርንበትን ዓላማ ዘንግተናል ማለት ነዉ፡፡
ሐ. በእምነት ያልሆነ ሁሉ ኃጢያት ነዉ (ሮሜ 14፡23) ፡፡ እግዚአብሔር ደግሞ ኃጢያትን ይጠላል፡፡ እግዚአብሔርን ማመን ባልቻልን ጊዜ ሁሉ እርሱ ሀሰተኛ እንደሆነ፣ የሰጠዉንም ተስፋ እንደማይፈጽም እየቆጠርነዉ ነዉ ያለነው ማለት ነው (ዘፍ. 23፡19) ፡፡
መ. አለማመን ወደ አለመታዘዝ ይመራናል ፡፡ የእግዚአብሔር ተስፋዎች እንዲፈጸሙ መታዘዝ አስፈላጊነዉ፡፡ለተገለጠልን የእግዚአብሔር ፈቃድ አለመታዘዝ ደግሞ በእግዚአብሔር አይን አመጽ ነዉ ፡፡
ሠ. እምነት የጻድቅ መኖሪያ ነው (ሮሜ.1፡17)
ረ. ያለእምነት በዚህች አለም ላይ በአሸናፊነትና በድል መኖር አይቻልም ዮሐ.5፡4)
ሰ. ያለእምነት ደስተኛ ሆኖ መኖር አይቻልም (1ጴጥ.1፡8-9)
ሸ. መንፈስ ቅዱስን መቀበል የሚቻለዉ በእምነት ነዉ (ገላ.3፡2)
ቀ. መጽደቅም በእምነት እንጂ በስራ አይደለም (ገላ.2፡16)
በ. ያለእምነት መጸለይም አንችልም (ያዕ.1፡6) መልስንም ከጌታ ኢየሱስ አንቀበልም (ማቴ.21፡22፡6፡11) ስለዚህ እምነት ለቁሳቁስ አቅራቦቶቻችንም ቁልፍ ነዉ፡፡
ተ. ሰውም ለመጠመቅ መጀመሪያ ማመን አለበት (ማር 16፡16) በእግዚአብሔር እምነት የሌላቸዉ ሁሉ የግድ በሌላ በአንድ ነገር ያምናሉ ማለት ነዉ፡፡ በኃይማኖት ወግ፣ በሳይንስ መረዳት፣ በተፈጥሮ መረጃዎች፣ በማስሚዲያዎች ወይም በእነዚህ ሁሉ
ቅንብር ያምናል (ሮሜ.1፡22) ፡፡ በእርግጥም ሙሉ በሙሉ በእግዚአብሔር የማያምኑ ሁሉ በአንድ ስፍራ በዳቢሎስ አምነዉ ራሳቸዉን ያገኙታል ፡፡ ሰይጣን እንዳለ ባለማመን እንኳን እያለ ሰዉ ሰይጣን የሚለዉን ማመንም ይቻላል ማለት ነዉ፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር በእርሱና በሚለን እንድናምን መፈለጉና መጠበቁ ጻድቅ ነዉ፡፡ እዉነትን ሊነግረን፣ ሊረዳንና ለህይወት ጥያቄዎቻችን
ሁሉ መልስን ሊሰጠን እርሱ የታመነ ነዉና፡፡
8.8. እምነትን በተግባር (በሥራ) ላይ ማዋል
መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያስተምረን እዉነተኛ የተፈተነ እምነት ‹‹በእሳት ምንም ቢፈተን ከሚጠፋዉ ወርቅ ይልቅ አብልጦ የሚከብር›› እንደሆነ ነዉ (1ጴጥ.1፡7) ፡፡ ስለዚህ በእምነት ህይወታችን ላይ ሊመጡ የሚችሉ ፈተናዎች እንዳሉ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ እምነትን በተገቢዉ መንገድ በተግባር ላይ ለማዋል የምንችለዉ፡-
ሀ. በማንኛዉም ጉዳዮቻችን በተመለከተ በእግዚአብሔር ቃል ዉስጥ የተገባልልን ኪዳን /ተስፋ መያዝ (ፊልጵ.4፡19፣2ቆሮ.1፡20) ፤
ለ. ተስፋዉ /ከኪዳኑ ጋር የተያያዙትን ቅድመ ሁኔታዎችን መፈጸም/ (1ዮሐ.5 ፣ዘዳ፡28፡1-3፣15፣ሚል.3፡7-12 (10) ፣ ማር.11፡24-25)፤
ሐ. የተስፋ ቃሎቻችን አምነን መናገራችንን (confession) ባለማቋረጥ መቀጠል ፤
መ. የሰማነዉን ቃል አድራጊዎች መሆን (ያዕ.1፡22-23፣ ዮሐ.9፡7፣ያዕ.2፡20-24) ፤
ሠ. ያመነዉንና የያዝነዉን እምነት በተግባር መለማመድ (ማቴ.9፡20-22 ፣14፡25-29) ፤
ረ. በራስ ማስተዋል አለመደገፍ (ምሳ.3፡1-6፡1ጢሞ.1፡4-7፡620-21፣ 2ጢሞ. 2፡16-18፣
ሮሜ.14፡1፣ቆላ.2፡8)
ሰ. ሰው ሲጠመቅ ያመነውን በሥራ ገለጸው ማለት ነው፡፡
8.9. የእምነት ጠላቶችን ድል መንሳት
እምነት በአማኞች ሕይወት እንዳይሰራና እንዳያድግ ከሚያደርጉት የእምነት ጠላቶች ዋናዎቹን እንደሚከተለዉ እንመለከታለን፡-
ሀ. አለማወቅ፡- ማንም ሰዉ ያልሰማዉንና ያላወቀዉን ተስፋ/ኪዳን ከእግዚአብሔር ዘንድ ሳይኖረዉ እምነት ሊኖረዉ ወይም እምነቱ ሊዳብር አይችልም ፡፡ ለዚህ ደግሞ መፍትሄዉ የእግዚአብሔርን ቃል ማጥናትና ማሰላሰልን ይጠይቃል ፡፡
ለ. ፍርሃት፡- ፍርሃት ክፉና መጥፎ ነገር ይደርስብኛል ብሎ በእዉነት ዕውቀት ላይ ያልተመሰረተ አሉታዊ ስሜት ነዉ (fear= false
evidence appearing real) ፡፡ በእግዚአብሔር አባታዊ ጥበቃ እና ፍቅር ላይ መታመን ያስፈልጋል (1ዮሐ.4:18) ፡፡
መጽሐፍ ቅዱስን እንዴት እናጥና?
በቅድሚያ ቃሉን ለማጥናት አእምሮዉን በመሰብሰብና አካባቢዎም ከረብሻ የጸዳ ቢሆን ይመረጣል፣ ቃሉን ሲያነብቡ ምስጢሩ እንዲገባዎት የቃሉን ባለቤት እውነቱን እንዲገልጥልዎት ይጸልዩ (መዝ. 118፡17-18) ፡፡
አስቀድመን እንደተመለከትነዉ ቃሉ በሕይወታችንም እንዲሰራና የሚሰጠንንም ጥቅም ለማግኘት የሚከተሉትን ዋናዋና መርሆች በመጠቀም መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ያስፈልገናል፡፡
ሀ. ቃሉን ለማጥናት ጊዜን መስጠት (ዕዝ.7፡10)
ለ. የቃሉን መንፈስና ዕዉነት በመግለጥ እንዲናገረንና እንዲያስረዳን አስተማሪ የሆነዉን የእግዚአበሔርን መንፈስ በጸሎት መጋበዝ (ዮሐ.14፡26፣16፡13-15)
ሐ. የልብ ፍላጎትና ፈቃደኝነት ይኑረን (1ኛጴጥ.2፡1-3፣የሐዋ.17፡10-11፣ኤር.15፡16)
መ. ማስተዋል (ዕብ.4፡1-2፣ማቴ.13፡14-15፣ኢያ33፡14፣37፡5፣የሐዋ.8፡27-31)
ሠ. በእነዚህ መንገዶች ያጠናነዉን ቃል፡-
• እናሰላስለዉ (meditation of the word)
• ትዝታችንም ይሁን (memorization of the word)
• ለግል ህይወትህ እንዲናገርህ ራስህን በማዘጋጀት የሚከተሉትን ጥያቄዎች ጠይቅ፡-
1. በማነበዉ ክፍል ዉስጥ ያለዉ ሃሳብ የእኔን ህይወት የሚመስልበት ሁኔታ አለን ?
2. ልከተለዉ የሚገባኝ ትምህርት፣ ምክር ወይም መመሪያ አለን ?
3. እንድናዘዘዉና እንድተወዉ የሚያሳየኝ ኃጢአት አለን ?
4. እንድጠብቀዉ የሚያሳየኝ ተስፋ አለን ?
5. ሌሎች ላስታውሳቸው የሚገባኝ እዉነቶች በዚህ ክፍል ዉስጥ አሉን?
ረ. ያገኘኸዉን መልእክት አጭር እና ግልጽ አድርገህ በማስታወሻህ ላይ ጻፈዉ
ሰ. የተገለጠልህን እዉነት ተግተህ ታዘዘዉና ተግብረዉ (1ኛሳሙ.15፡22-23፣ያዕ.1፡22-25፣ዮሐ.8፡31-32)
ሸ. እንደአስፈላጊነቱ ለሌሎች አካፍለዉ፡፡
እንግዲህ በዚህ መንገድ ቃሉን ተረጋግተዉ ማጥናት የሚችሉ ሲሆን ከመጸሐፍ ቅዱስ ጋር ያለዎት
ዝምድና ቀላል እንዲሆን የብሉይ ኪዳንና አዲስ ኪዳን መጸሐፍት ዝርዝርን በቃል ቢያጠኑ ቶሎ ብለዉ የሚፈልጉትን ለመግለጽና ለማውጣት አይቸገሩም ፡፡ በተጨማሪ የግዕዝ ቁጥሮችን ቢያጠኑ ጥሩ ነዉ፡፡ ቁጥሮቹን ለማጥናት ብዙ ሳይደክሙ፡-
ከ1-10 እና 20፣ 30፣ 40፣ 50፣ 60፣ 70፣ 80፣ 90፣ 100 እና 1000 እንዴት ዓይነት ቅርጽ እንዳላቸዉ ለይተዉ ይወቋቸዉ፡፡
1፣ 2፣ 3፣ 4፣ 5፣ 6፣ 7፣ 8፣ 9፣ 0፣ !፣ “፣ #፣ $፣ %፣ &፣ ‘፣ (፣ )፣ *
3.1. የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ አጠናን ዘዴዎች
መጽሐፍ ቅዱስ በመጀመሪያ ሲጻፍ ምንባቡ የነበረውን ትክክለኛ ትርጉም ለማግኘት የተቻለውን ሁሉ ጥረት ማድረግ ከአጥኚው ይጠበቃል፡፡ ይህም አጥኚው ከልዩ ልዩ አውዶች አንጻር ማየትን ያካትታል፡፡
ምሳሌ፡-
• ታሪካዊ ዐውድ
• ባህላዊ ዐውድ
• ቋንቋዊ ዐውድ
• ፖለቲካዊ ዐውድ
• ማህበራዊ ዐውድ
• ኃይማኖታዊ ዐውድ
መጸሐፍ ቅዱስን ሰዎች በተለያየ መንገድ ሊያጠኑ ይችላሉ፡፡ አጠናንዎን በተለያየ መንገድ እስኪያሰፋ ግን በእነዚህ በሶስት መንገዶች ማጥናት ቢችሉ ይመረጣል፡፡
3.2. ሶስቱ የጥናት መንገዶች
ሀ. ምዕራፍ በምዕራፍ የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት ፣
ለ. በሰዎች ሕይወት ላይ የተመረኮዘ ጥናት ፣
ሐ. በተወሰነ ርዕስ ላይ የሚደረግ ጥናት ናቸዉ፡፡
ሀ/ ምዕራፍ በምዕራፍ የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት ከመጸሐፍ ቅዱስ አንድን መጸሐፍ በመዉሰድ በየእለቱ አንድ ምዕራፍን ሲወስኑ እነዚህን መሰረታዊ ጥያቄዎች በመጠየቅ ማጥናት ይቻላል፡፡
• ለምዕራፉ ምን ርዕስ ይሰጠዉ
• በምዕራፉ ዉስጥ የተሰጡ ዋናዋና ትምህርቶች ምንድን ናቸዉ
• በምዕራፉ ዉስጥ ልብህን የነካዉ ጥቅስ ምንድን ነዉ ጽፈህ በቃልህ እስክትይዘዉ ድረስ ደጋግመህ አጥናዉ
• በምዕራፉ ዉስጥ የተጠቀሱትን ዋናዋና ሰዎችን ጥቀስ
• በምዕራፉ ዉስጥ ስለ አማላክ ማንነነት ባህርይ የተጠቀሰ ካለ ግለጽ
• እኔ ልከተለዉ የሚገባኝ ምሳሌ ምንድን ነዉ
• እኔ ላስወግደዉ የሚገባኝ ስህተት ምንድን ነዉ
• እኔ ልፈጽመዉ የሚገባኝ ትዕዛዝ ምንድን ነዉ
• እኔ ልይዘዉ የሚገባኝ የተስፋ ቃል ምንድን ነዉ
• በዚህ ምዕራፍ መሰረት ልጸልየዉ የሚገባኝ ጸሎት ምንድን ነዉ
በእነዚህ ከላይ በተሰጡት መጠይቆች መሰረት በማጥናት ማወቅ የሚቻል ሲሆን የተሰጡትን ጥያቄዎች በሙሉ በምዕራፍ ዉስጥ ላይመለስ ይችላል፡፡
ለ/ በሰዎች ህይወት ላይ የተመሰረተ ጥናት
በመጸሐፍ ቅዱስ ዉስጥ 2330 ሰዎች ገደማ ተጠቅሰዋል ፤ ከእነዚህም ብዙዎቹ የህይወት ታሪካቸዉን በመከታተል ብዙ ትምህርት ልናገኝ እንችላለን፡፡ ከመጽሐፍ ቅዱስ የሆነ የሰዎችን ወይም የስፍራን ስም በመዉሰድ ማጥናት ፣ ለምሳሌ ፡- “ሄሮድስ” ይህ ስም ስንት ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ ዉስጥ ተጠቅሷል መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ሰዉ ምን ይላል ? ይህ ማለት የአንድን ሰዉ (ገፀ ባህሪይ) የህይወት አቋሙን ማጥናት ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ፡- ስለ “ዳዊት” — ከእግዚአብሔር ጋር የነበረዉን ግኑኝነት፣ ለእግዚአብሔር መሰጠቱ፣ የሠራዉ መልካምነት ወዘተ.
በዚህ ጥናት ዉስጥ የሰዎቹን ስምን ትርጉም ለማወቅና ታሪኩ ጎልቶ እንዲገባን የመጸሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት በተጨማሪ ቢኖረን ይመርጣል፡፡ ይህን ጥናት ለማጥናትም ከዚህ በታች ያሉትን ጥያቄዎች መመለስ ያስፈልጋል፡፡
• ስለሰዉየዉና ስለቤተሰቡ ምን ተጻፈ
• በወጣትነቱ ዘመን ምን አከናወነ
• በህይወቱ ዘመን የገጠመዉ ፈተና ምን ነበር እንዴትስ ተወጣዉ
• ሰዉየዉ ከእግዚአብሔር ጋር በነበረዉ ግንኙነት የታየዉን ስጋዊ ድክመት ይግለጹ
• በእምነቱ ጽናት የተገለጸዉ የእግዚአብሔር ክብር ምንድን ነዉ
• ጓደኞቹ እነማን ነበሩ ጓደኞቹ በህይወቱ ላይ ምን አይነት ለዉጥ አመጡ
• በህይወት ዘመኑ የተሳሳታቸዉ ነገሮች ምንድን ናቸዉ
• ሰውየው ክርስቶስን ይመስል ነበር ወይስ አይመስልም
• በሰዉየዉ ህይወት ላይ ይታዩ የነበሩ መልካም ስነምግባሮችን ይግለጹ
• ከዚህ ሰዉ ህይወት ያገኙትንና ለትምህርትዎ የሚሆኑ ዋናዋና አሳቦችን ይግለጹ
በጥናቱ መሰረት ጸሎትን ይጸልዩ፡፡
ሐ. በተወሰነ ርዕስ ላይ የሚደረግ ጥናት
ይህ ጥናት ደግሞ ከመጸሐፍ ቅዱስ ዉስጥ ልታጠናዉ የፈለግነውን አንድን ርዕስ (topic) በመዉሰድ በርዕሱ መሰረት ሰፊ ጥናትን ማካሄድ ነዉ፡፡ ለምሳሌ፡- ጸሎት፣ ንስሃ፣ ቅድስና፣ ፍቅር፣ እምነት፣ ወዘተ … ለዚህ ጥናትም የተለያዩ የማጥኛ መረጃ እንደ የመጸሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላትና ሌሎች ኮሜንታሪ መጽሐፍትን፣ እንዲሁም የመጸሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ማዉጫ ቢኖርም ይመረጣል፡፡
የሚፈልጉትን ርዕስ ከመረጡ በኋላ በተለያየ ስፍራ ስለ ርዕሱ የተሰጡትን ጥቅሶች በማገናዘብ ማጥናት ይቻላል፡፡
ለምሳሌ፡- ርዕስ፡- ጸሎት፤
– ወደ ማን እንጸልይ
– መቼ እንጸልይ
– እንዴት እንጸልይ
– ምን እንጸልይ ወዘተ የመሳሰሉትን ጥያቄዎች በመመለስ ጥናትዎን ያስፉት፡፡
በአጠቃላይ እነዚህን የግል የመጸሐፍ ቅዱስ ማጥኛ ዘዴዎችን መጠቀም የሚቻል ሲሆን እዉቀትዎን የበለጠ ለማስፋት በአጥቢያዎ የሚሰጡትን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርችን ቢከታተሉ ያግዝዎታል፡፡
እግዚአብሔርን ማወቅ – ክፍል …..7…..
. እግዚአብሔርን ፍለጋ – ቀጣይ፡-
ምኑን ነው የምንፈልገው?፡-
ባለፈው ክፍል – እግዚአብሔርን ፍለጋ በሚል – ስለእግዚአብሔር መኖር በተፈጥሮ፣ በሕሊና፣ በመሳሰሉት ማረጋገጥ እንደሚቻል አይተናል።
በአሁኑ ጊዜ የፈጣሪን /የእግዚአብሔርን መኖር የሚጠራጠር ብዙም ላይኖር ይችላል፤ ወይም በአሁኑ ጊዜ ለኛ ይህ ብዙም አሳሳቢ ጥያቄ አይደለም።
ከላይ ከተጠቀሱት በአንዱ ወይም በሌላ በሆነ መንገድ – የእግዚአብሐየርን መኖር አረጋገጥን – እግዚአብሔርን አገኘነው። ካገኘነው በኋላ ምኑን ነው ማየት የምንፈልገው? ስንል ዳዊት እንዲህ ይለናል፡-
ሁልጊዜ ፊቱን ፈልጉ። መዝ ፻፬/፻፭፣ ፬
– የእግዚአብሔር ሕልውና /መኖሩ/ የሚረጋገጠው አንድ ጊዜ ነው። ከተገኘ – አለ። አይጠፋም።
ከዚያ በኋላ ግን ሁልጊዜ መፈለግ ያለብን – ፊቱን – ነው።
– በምናያቸው ፍጥረታት የእግዚአብሔርን አስደቂ ኃያል እጅ እናያለን። ቀጥሎ ግን ሁልጊዜ ፊቱን ማየት አለብን።
ፊት ምንድን ነው? -የማንነት መለያ ነው። ሁላችንም የምንለየው በፊታችን ነው። መታወቂያ ላይ የሚደረገው ፎቶ – ጉርድ ፎቶ – የሚያሳየው ፊታችንን ነው።
– አንድን ሰው አየሁት ለማለት – ፊቱን – ማየት ግድ ነው።
– ሙሴ ከእግዚአብሔር ጋር ሕዝቡን ነጻ አውጥቶ ሲመራ፣ በተአምራት ብዙ ዘመን ከኖረ በኋላ፡- እግዚአብሔርን እንዲህ ሲል ጠየቀው፡-
o እርሱም፦ እባክህ ክብርህን አሳየኝ አለ።….
– እግዚአብሔርም –
o …ሰው አይቶኝ አይድንምና ፊቴን ማየት አይቻልህም……ፊቴ ግን አይታይም» አለ። ዘጸ ፴፫፡ ፲፯ – ፳፫።
– ፊቱን ማየት የማይቻል ከሆነ -ፊቱ የማይታይ ከሆነ – ለምን ፊቱን ፈልጉ ተባለ? – ማየት የማይቻለው በዚህ በሥጋ ዓይን ነው። እግዚአብሔር መንፈስ ነውና።
– በመንፈስ ግን ከእኛ ጋራ ሲሆን፣ ሲሠራ፣ ሕይወታችን ሲጠብቅ… እናየዋለን።
ከእያንዳንዳችን የራቀ አይደለም። (የሐዋ ፲፯፣ ፳፮)
– መምህራን እንደሚያስተምሩት በርግጥ የሙሴ ጥያቄ ተመልሷል፤ ነገር ግን የተመለሰው ከ1400 ዓመት በኋላ- በኢየሱስ ክርስቶስ – በደብረ ታቦር ነው።
o ሙሴ በጥየቄው መሰረት በዓይነ-ሥጋ በአካል እግዚአብሔርን ያየው – በኢየሱስ ክርስቶስ – ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ በስጋ የተገለጠው አግዚአብሔር ነውና።
በፊታቸውም ተለወጠ፥ ፊቱም እንደ ፀሐይ በራ፥ ልብሱም እንደ ብርሃን ነጭ ሆነ። እነሆም፥ ሙሴና ኤልያስ ከእርሱ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው። ማቴ ፲፯፣ ፪ – ፫
ዛሬም እኛ እግዚአብሔርን በመንፈስ ዓይን የምናየው – በኢየሱስ ክርስቶስ ነው።
ስለዚህ፡-
፭. የፍለጋው ማብቂያ – ኢየሱስ ክርስቶስ
o በተሰጠን አእምሮ በምናደርገው ምርምር በተፈጥሮ፣ በኅሊና.. ፈጣሪ እንዳለ እናውቃለን። ፍጥረታትን ሁሉ እግዚአብሔር እንደፈጠራቸው እንዳስገኛቸው እንደሚቆጣጠራቸው እንረዳለን።
o እግዚአብሔርን ፍለጋ የምናደርገው ጥረት እግዚአብሔር እንዳለ እንድናውቅ እንጂ ከእግዚአብሔር ጋር እንድንገናኝ አያደርገንም።
o ከእግዚአብሔር ጋር የምንገናኘው በእኛ ፍለጋ ሳይሆን በእርሱ ፍለጋ ነው። እርሱ እኛን ስለፈለገን። ስለዚህ የእኛ እግዚአብሔርን ፍለጋ የሚጠናቀቀው በራሱ በእግዚአብሔር ፍለጋ ነው።
– የእግዚአብሔር ፍለጋ – ፍለጋው አያልቅም – እንደምንለው አይደለም። መድረሻ አለው። የእግዚአብሔር ፍለጋ ማብቂያው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።
እኛ እርሱን ልንደርስበት ስለማንችል እርሱ እኛን ፈለገን። በሚገባን በምናውቀው ባሕርይ። በሰው – ሰው ሆኖ ሊፈልገን መጣ።
የሰው ልጅ የጠፋውን ሊፈልግና ሊያድን መጥቶአለና አለው። ሉቃ ፲፱፣ ፲
መቼም ቢሆን እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ የለም፤ በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ እርሱ ተረከው። ዮሐ ፩፣ ፲፰።
ተረከው – ማለት የቃል ትረካ አይደለም፤ በተግባር በኑሮ፣ በሕይወት፣ በሞት፡በትንሣኤ… ገለጠው ማለት ነው።
ክርስቶስን ስናገኝ / ክርስቶስ ሲያገኘን/ ያን ጊዜ እግዚአብሔርን አገኘነው – አወቅነው፡ ማለት ነው።
ማጠቃለያ፡- እግዚአብሔር አንዲህ አለ / ብሎ ተናገረ፣ ከማለታችን በፊት እግዚአብሔር አለ /መኖሩን/ እንበል።
– እግዚአብሔር አለ/የለም በሚል ክርክር አንዱ ፈላስፋ የቆሎ ተማሪን ሲጠይቀው፣ እነዲህ መለሰለት፡ «እግዚአብሔርን አለ ብለኽው ባይኖር ችግር የለውም፤ የለም ብለኽው ካለ ግን ወዮልህ።»
– አንዳንድ ወገኖች – ከባድ ችግር ሲገጥማቸው ወይም ያልሆነ መጥፎ ነገር ሲያዩ «እግዚአብሔርማ የለም፤ በእውነት ቢኖር እንደዚህ አይሆንም ነበር፤ » ይላሉ።
– እግዚአብሔር አንድን ነገር ለምን እንደሚያደርግ፣ እንዴት እንደሚሠራ ለእኛ ሁሉም ነገር ግልጽ ላይሆን ይችላል። ዝም ብለን በትዕግስት እንጠብቀው፤
እንደሚባለው አንዳንድ ነገሮች በጣም እንግዳ ይሆናሉ፤ ለምን እንዲህ ይሆናል አንበል፤ ቃሉ እንደሚል፡-
ምሥጢሩ ለአምላካችን ለእግዚአብሔር ነው የተገለጠው ግን የዚህን ሕግ ቃሎች ሁሉ እናደርግ ዘንድ ለእኛ ለዘላለምም ለልጆቻችን ነው። ዘዳ ፳፱፣ ፳፱
– ያለማቋረጥ ፀሐይን የሚያወጣት/የሚያገባት፣ ዝናቡን የሚያዘንብ፣ አዝመራውን የሚያበቅል፣ ለፍሬ የሚያደርስ፣ ሁሉን የሚመግበው ፣ የሚያስተዳድረው አምላክ – አለ።
– እኛንም ወደዚች ምድር ያመጣን፣ የፈጠረን ነው እርሱ የሚያኖረን ። አንጨነቅ።
– በእውነት እግዚአብሔር አለ ። ከሁሉም በላይ ትልቅ መጽናኛችን ነው።
o መኖሩን ያመንነውን – ፈልገን ያገኘነውን ወይም በትክክል ለመናገር ፈልጎን ያገኘንን / እንድናገኘው የተፈለገውን/ መተዋወቅ ቀጣዩ ተገቢ ጉዳይ ነው ። ስንተዋወቅ የምንለዋወጠው ስምን ነው? — እገሌ እባላለሁ።- –
o ስለዚህ ይህ ፈጣሪ ማን ይባላል?….
o የእግዚአብሔር ስም.. ይቀጥላል
እግዚአብሔርን ማወቅ – …..6…..
እግዚአብሔርን ፍለጋ – ቀጣይ
፫. የት ነው የምንፈልገው?
፫.፩ በተፈጥሮ፡- ለእግዚአብሔር ሕልውና የመጀመሪያው ማስረጃ ሥነ ፍጥረት ነው።
የማይታየው ባሕርይ እርሱም የዘላለም ኃይሉ ደግሞም አምላክነቱ ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ ከተሠሩት ታውቆ ግልጥ ሆኖ ይታያልና፤ ሮሜ ፩፣ ፳
እየመረመሩ ከተባለ – ለመመርመር ስሜት ህዋሳቶቻችንን እንጠቀማለን። ከእነዚህም አንዱ እና ዋናው ማየት ነው። ምን እናያለን? የምናየው ምንድን ነው?
ሀ. ፍጥረታት ከምን ተገኙ? ከየት መጡ? የሚታየው ነገር ሁሉ አስገኚ አለው። በራሱ የተገኘ ነገር የለም።
o አንዳንድ ወገኖች ዓለሙ የተገኘው እንዲሁ ነው የሚሉ አሉ፤ – ተመራማሪዎች።
§ በእግዚአብሔር መኖር የማያምን ጓደኛ የነበረው አንድ የእግዚአብሔር ሰው ያን ኢአማኒ ጓደኛውን «ዓለማት ከየት ተገኙ?» ሲለው
የማያምነው ጓደኛም፡- «እንዲሁ ተገኙ» ይለው ነበር።
አንድ ቀን አማኙ በካርቶን እና በወረቀት ቆንጆ ቤት ከሠራ በኋላ ጠረጴዛው ላይ አስቀመጠው። በኋላ ከሃዲ ጓደኛው ሲመጣ የቤቱን ሞዴል አይቶ በጣም ተደነቀና ፡- « ከየት አገኘህው?» ሲለው – አማኙ «እንዲሁ ተገኘ» አለው.. ይሄማ ሊሆን አይችልም ሲል ያ አማኙ ጓደኛም፡- «አየህ እኔም ፍጥረታት ከየት ተገኙ? » ስልህ እንዲሁ ስትለኝ የነበረውም ሊሆን አይችልም ማለት ነው።
§ የምናየው ነገር ሁሉ ሠሪ ወይም አስገኝ አለው። በራሱ የተገኘ ነገር የለም። ወንበሩ- አናጺ፣ ቤቱ-ግምበኛ… ሁሉም የየራሱ አስገኚ የሆነ ባለሙያ አለው። በአጠቃላይ የዚህ ውብ ተፈጥሮ አስገኝውስ ማን ነው? ስንል -ፈጣሪ- እንዳለ /እንዳለው እንረዳለን።
ለ. ፍጥረታት እንዴት ተገኙ?
o አሁንም ተመራማሪዎች የመጀመሪያው ታላቅ ፍንዳታ (Big Bang) ከተከሰተ በኋላ- በሂደት ነገሮች ሁሉ ተገኙ፤ ይላሉ። ግን የመጀመሪያው የታላቅ ፍንዳታ ቁስ ከየት መጣ? ሲባል መልስ የለም።
ከዚያም በኋላ በአዝጋሚ ለውጥ- አንዱ ከአንዱ እየተወጣ.. ተገኙ ይላል።
o አንድ ጸሐፊ እንዲህ ብሏል፡- ነገሮች አንዱ ከአንዱ ተገኘ ከተባለ ይህ ማለት እንግዲህ በከተማችን የምናያቸው ታላላቅ ፎቆች፣መንገዶች፣ ድልድዮች የተገኙት፡- ጥሬ ዕቃዎቹ – ብረቱ፣ ሲሚንቶው ራሳቸውን አዘጋጅተው፣ እንጨቶች ራሳቸውን ጠርበው አስተካክልው፣ ጡቦች በራሳቸው እየተደረደሩ፣ ቆርቆሮው በራሱ እየተመታ፣ እየተጋጠመ ቤቱ ተሠራ የማለት ያህል ነው። ይህ ግን ፈጽሞ የማይሆን ነገር ነው።
o ይህ ዓለም የተፈጠረ ብቻ ሳይሆን በሥርዓት የተዋቀረ ዓለም ነው። Intelligent design – ግሩም ንድፍ ያረፈበት ድንቅ ተፈጥሮ ማለት ነው።
ሐ. ፍጥረታት እንዴት ይኖራሉ?
o ፍጥረት ሁሉ በእንቅስቃሴ ላይ ነው። የፀሐይ መውጣት/መግባት – የምድር መዞር- የፕላኔቶች – .. ሁሉም በእንቅስቃሴ ላይ ነው። ማን ነው የሚያንቀሳቅሰው? ወይም ይህንን እንቅስቃሴ የሚመራው/ የሚቆጣጠረው ማን ነው?
§ ምድር፡- በፀሐይ ሥርዓት ውስጥ ፣ ወይም በሕዋ ውስጥ ያላት ሥፍራ ሕይወትን ሊያኖር በሚችል መልኩ የተቀመጠች ናት። ምድር በፀሐይ ዙርያ ስትዞር ከምሕዋሯ ትንሽ ራቅ ብትል – ሁሉም ነገር በረዶ ሆኖ በከፍተኛ ቅዝቃዜው ሕይወት በሙሉ ይሞታል፤ በተመሳሳይ ከምሕዋሯ ትንሽ ቀረብ ብትል በከፍተኛው ሙቀት የተነሳ ሁሉም ይቀልጥና ሕይወት አይኖርም፡።
§ ሕይወት ላላቸው ፍጥረታት ሁሉ ወሳኝ የሆነው – ውኃ – በሶስቱም ኩነቶች የሚገኘው በምድር ብቻ ነው። – / በጠጣርነት (በረዶ)፣ በፈሳሽነት (ውሃ) እና በእንፋሎት (ተን)/ ። ስለዚህ ከምድር ውጪ ሕይወት ያለው ነገር እስካሁን በሌሎች ዓለማት /ፕላኔቶች/ ማግኘት አልተቻለም።
፫.፪ በሕሊና፡-
§ በተፈጥሮ ሀሉም ሰው ክፉና ደጉን የመለየት ሚዛናዊነት ተቀምጦለታል። ሰው ቢማርም ባይማርም፣ እግዚአብሔርን ቢያምንም ባያምንም በተፈጥሮው በሕሊናው መልካም ና መጥን የመለየት ችሎታ አለው። ይህ የሕሊና ዳኝነት – እንዴት በሁላችን ውስጥ ሊኖር ቻለ? ማን አስቀመጠው? – የጋራ ነገር እንዲኖረን ያደረገ አንድ አካል አለ?– አዎ እርሱም የፈጠረን እግዚአብሔር ነው።
ü ሰው ሥጋ /matter/ ብቻ አይደለም መንፈስ /Spirit/ አለው። ቁሳዊ ነገር ከቁሳዊ ነገር ሊገኝ ይችላል። ነገር ግን መንፈሳዊ ነገር ከቁሳዊ ነገር ሊገኝ አይችልም። መንፈሳዊ ነገር ከመንፈስ ብቻ ነው ሊገኝ የሚችለው። — እርሱም እግዚአብሔር ነው።
ü ስሜታዊ ነገሮች ፡ – ደስታ፣ ፍቅር፣ ሠላም፣ እምነት … የምንላቸው ማኅበራዊ እሴቶች ከቁሳዊ ነገር ሊገኙ አይችሉም። እነዚህን የማይዳሰሱ ረቂቅ ስሜቶችን ያስገኘ ስሜት ያለው / የሚሰማው/ ነው። — እርሱም እግዚአብሔር ነው።
ü ፫.፫ በጠፈር ምርምር
እስከዛሬ ያልተደረሰባቸው ብዙ ፍጥረቶች ።
o ስለከዋክብት ብዛት በሳይንሱ የሚሰጠውን መግለጫ ብናይ፡-
ü በዘመናዊ ግዙፍ የርቀት ማሳያ /ቴሌስኮኘ/ ተመርምሮ እንደተገኘው ከኛ ፀሐይ አካባቢ የሚገኙ ከዋክብት ቁጥራቸው እስከ ሀያ ሚሊዮን ይጠጋል፡፡ ያለመሣርያ በባዶ ዓይን ሲመለከቷቸው ግን አምስት ሺህ ብቻ ያህላሉ ይላሉ፡፡
ü ተመራማሪዎቹ እንደሚሉት የከዋክብት ቁጥራቸው ሊወሰን የማይችል እልፍ አእላፍ /የብዙ ብዙ/ ስለሆነ የብዛታቸው ልክ እንኳንስ ተቆጥሮ ሊደረስበት ይቅርና ታይቶ የማያልቅ ነገር ሆኖባቸዋል፡፡ የርቀት መሣርያ መነጽሩን /ቴሌስኮኘ/ አሠራርና የማስተዋሉንም አኳኋን እያሻሻሉ በሄዱበት መጠን ቀድሞ ያልታዩ ሌሎች አዳዲስ ከዋክብት ይገኛሉ፡፡
ü የዚህን ሁኔታ ሲናገሩም መነጽሮቻችን ምንም ያህል ብናሻሽላቸው ከዋክብትን ጨርሰን ሙሉ በሙሉ ልናያቸው አንችልም፡፡ በጣም ዘልቀን ለማየት በቻልንበት መጠን ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሌሎች አዳዲስ ከዋክብት ይወጣሉ፡፡ የእኛ ዕውቀት ከቶ ሊዘልቀው የማይቻል ነው ይላሉ፡፡ /የዕውቀት ብልጭ ፤ ከበደ ሚካኤል፡ ገጽ 158/
o ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ፥ የሰማይም ጠፈር የእጁን ሥራ ያወራል። መዝ ፲፰/፲፱፣ ፩
የሰማይ ጥልቀት / የየከዋክብቱ ርቀት/፣- አሁንም ለዚህ የሳይንሱን መግለጫዎች ብናይ፡-
ü በፀሐይና በመሬት መካከል ያለው ርቀት ወደ 150 ሚሊዮን ኪ.ሜ ይጠጋል፡፡ የርቀቱን ግምት ለመገንዘብ በመድፍ ጥይት ጉዞ መስለው ይናገራሉ፡፡ የመድፍ ጥይት ፍጥነቱን ሳይቀንስ ከምድር ወደ ፀሐይ ቢተኮስ ከፀሐይ ለመድረስ 20 ዓመት ይፈጅበታል፡፡ ይህም ፀሐይ ከመሬት ምን ያህል በጣም የራቀች መሆኗን ያሳየናል፡፡
ü በማታ ከምናያቸው ስፍር ቁጥር ከሌላቸው በርካታ ከዋክብት ውስጥ ለመሬት ቅርብ የሆነችው ኮከብ ከላይ በተቀመጠው ምሳሌ መሠረት ርቀቷ እጅግ በጣም ብዙ ከመሆኑ የተነሳ የመድፍ ጥይቱ ወደዚች ኮከብ ቢተኮስ ከርሷ ለመድረስ 7 ሺህ ዓመ ት ይወስድበታል፡፡
ü በዚህ ልኬታ የሌሎችን ከዋክብት ርቀት ብናስብ ምን ያህል የማይደረስበት እንደሚሆን መገመት እንችላለን፡፡ በየከዋክብቱ መሀል ያለው ርቀትም እጅግ በጣም ሰፊ ከመሆኑ የተነሳ የሚለካው ብርሃን ከነርሱ ለመድረስ በሚፈጅበት ጊዜ ነው፡፡ ይህም የብርሃን ዓመት ይባላል። ….
እግዚአብሔር በሰጠን አእምሮ – እየተመራመርን- ይሄን ሁሉ ስናይ /ስንሰማ/ የእነዚህ ሁሉ ፈጣሪ ምን ያህል ግሩም ድንቅ ነው እንድል ያደርገናል።
ü ከተፈጥሮ ሕግ ውጪ የሆኑ በሳይንስ ሊረጋገጡ /ሊመለሱ ያልቻሉ ብዙ ጉዳዮች /ክስተቶች አሉ።
o የአጋንንት እና የመናፍስት አሠራር ፤ ተአምራት፣ ድንቆች….
o የነፍስ ምንነት፣ ሞት ምንድን ነው? ወዘተ…
እነዚህ ሁሉ የሚያሳየን ሁሉን የፈጠረ፣ ሁሉን የሚቆጣጠር እና የሚመራ አምላክ እንዳለ ነው። ታዲያ የእግዚአብሔርን መኖር በተፈጥሮ፣ በሕሊና ፣ በመሳሰሉት… ካረጋገጥን በኋላ የምንፈልገው ምኑን ነው?
… /ይቀጥላል/
እግዚአብሔርን ማወቅ – …..5…..
እግዚአብሔርን ፍለጋ
ምናልባትም እየመረመሩ ያገኙት እንደ ሆነ፥ እግዚአብሔርን ይፈልጉ ዘንድ በምድር ሁሉ ላይ እንዲኖሩ የሰውን ወገኖች ሁሉ ከአንድ ፈጠረ፥ የተወሰኑትንም ዘመኖችና ለሚኖሩበት ስፍራ ዳርቻ መደበላቸው። ቢሆንም ከእያንዳንዳችን የራቀ አይደለም።
ከእናንተ ከባለ ቅኔዎች አንዳንዶች ደግሞ። እኛ ደግሞ ዘመዶቹ ነንና ብለው እንደ ተናገሩ፥ በእርሱ ሕያዋን ነንና እንንቀሳቀሳለን እንኖርማለን። የሐዋ ፲፯፣ ፳፮ – ፳፰
፩. እግዚአብሔርን መፈለግ ለምን አስፈለገ?
ü የተፈጠርንበት ዋና ዓላማ በመሆኑ- እግዚአብሔርን ይፈልጉ ዘንድ፡-
· የሰውን ወገኖች ከአንድ ፈጠረ – ከአዳምና ከሔዋን። አንድ ጊዜ ፈጠረ፣ በኋላ ብዙ ተባዙ ባለው አምላካዊ ቃል በመዋለድ የሰው ዘር ይቀጥላል።
o …..እግዚአብሔርም ባረካቸው፥ እንዲህም አላቸው፦ ብዙ፥ ተባዙ፥ ምድርንም ሙሉአት፥ ዘፍ ፩፡ ፳፯ – ፳፰
o አዳምም ለሚስቱ ሔዋን ብሎ ስም አወጣ፥ የሕያዋን ሁሉ እናት ናትና። ዘፍ ፫፣ ፳
· የምንኖርበትን ዘመን – እና – ስፍራ /ቦታ/ መደበልን። በየት ዘመን እስከ ስንት ጊዜ፣ በየት ሃገር ከየትኛው ቤተሰብ እንደምንወለድ እድሜና ሥፍራ የመደበልን እግዚአብሔር ነው።
ስለዚህ «አፄ /አቶ እገሌ ያለዘመናቸው የተወለዱ… » የምንለው ፈጽሞ ስህተት ነው ማለት ነው።
· እግዚአብሔር ሰውን የፈጠረበት ዓላማ እንዲፈልገው ነው። በሰጠው ነጻነት ተጠቅሞ ፈልጎ፣ አግኝቶ ፣ ወዶ እንዲከተለው እና አብሮት እንዲኖር።
· እግዚአብሔርን ስለመፈለግ ዳዊት እንዲህ ብሏል፡-
· …. በቅዱስ ስሙ ተጓደዱ እግዚአብሔርን የሚፈልግ ልብ ደስ ይበለው።
እግዚአብሔርን ፈልጉት ትጸናላችሁም ሁልጊዜ ፊቱን ፈልጉ። መዝ ፻፬/፻፭፣ ፩ – ፬
እግዚአብሔርን የምንፈልገው ለምንድን ነው? ከላይ በጥቅሱ እንዳየነው፡-
ü ልብን ደስ ስለሚያሰኝ፣- እግዚአብሔርን የሚፈልግ ልብ ደስ ይበለው
o ዘላቂ እና ከውስጥ – ከልብ – የሆነ እውነተኛ ደስታ ያለው እግዚአብሔርን በመፈለግ ነው። በሌላም ቦታ እንዲህ ተብሏል፡-
§ ሁልጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ፤ ደግሜ እላለሁ፥ ደስ ይበላችሁ። ፊልጵ ፬፣ ፬
ü ለመጽናት፣- እግዚአብሔርን ፈልጉት ትጸናላችሁም፡
o አንድ ሰው በተቸገረ ጊዜ – እገሌን ነው የምፈልግ እርሱ ይምጣልኝ – ይላል።
በፈተና በሕይወት ውጣ ውረድ ለመጽናት የሚረዳን የሚያስፈልገን እግዚአብሔር ብቻ ነው።
ü ለሚፈልጉት ምላሽ ስለሚሰጥ፣- እግዚአብሔር እርሱን ለሚፈልጉት ምላሽ ይሰጣል እንጂ ተደብቆ አይቀመጥም።
ያለ እምነትም ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ እግዚአብሔር እንዳለ ለሚፈልጉትም ዋጋ እንዲሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋልና። ዕብ ፲፩፣ ፮
o በፍለጋ ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ ሁለት ነገር ማመን አለበት፡
§ ፩. እግዚአብሔር እንዳለ – እግዚአብሔር አለ።
§ ፪. ለሚፈልጉትም ዋጋ ይሰጣል። – ይመልሳል። ይገናኛል።
– ፈልጉት ስንባል ሩቅ ወይም ረቂቅ ስለሆነ ግን አይደለም። ምክንያቱም – ከእያንዳንዳችን የራቀ አይደለም። ተብሏልና፤ ስለዚህ ቅርብ ነው።
– በምናየው በተፈጥሮ፣ ዓለምን በማስተዳደሩ /በመግቦቱ/ ፣ በነፍሳችን ጥማት… እግዚአብሔርን መፈለግ ግድ ይላል። እግዚአብሔር የራቀ / ሩቅ/ የሚሆነው ዓይነ-ልቦናችን በኃጢአት ጨለማ ሲያዝ ብቻ ነው።
– ማንም ሰው ከአምልኮ ውጪ አይደለም፤ ከእግዚአብሔር / ከአምላክ/ ፍለጋ ተለይቶ አያውቅም። ሁሉም ሰው የሚታመንበት፣ ተስፋ የሚያደርገው፣ አንድ አካል ይፈልጋል። እግዚአብሔርን የማያውቁና የማያምኑ ሰዎች እንኳን -ጨርሶ እምነት የለሽ- አይደሉም። የሚታመኑበት ይለያይ እንደሆነ እንጂ የሆነ አንድ የሚታመኑበት ነገር አላቸው፤ – ጣኦት፣ ሃብት፣ ….
– እግዚአብሔርን ፍለጋ አስፈላጊነቱ /አንገብጋቢነቱ/- በጨለማ ውስጥ መብራት የመፈለግ ያህል ነው። ካለዚያ የሚታይ ነገር አይኖርም፣ የሕይወት ጉዞው መደናበር ነው የሚሆነው። ሕይወት ያለእግዚአብሔር ጨለማ ናት።
እግዚአብሔር ብርሃን ነው ጨለማም በእርሱ ዘንድ ከቶ የለም የምትል ይህች ናት። ፩ ዮሐ ፩፣ ፭
፪. እግዚአብሔርን እንዴት ነው የምንፈልገው?
ü በአእምሮ፡- /በዕውቀት/ – ምናልባትም እየመረመሩ
o ምናልባት ለምን ተባለ? በተሰጠን አእምሮና ነጻ ፈቃድ በምናደርገው ምርምር እግዚአብሔርን ላንደርስበት እንችላለን። በዓለማዊ ጥበብና ምርምር ብቻ እግዚአብሔርን ማግኘት አይቻልም።
በእግዚአብሔር ጥበብ ምክንያት ዓለም እግዚአብሔርን በጥበብዋ ስላላወቀች፥ በስብከት ሞኝነት የሚያምኑትን ሊያድን የእግዚአብሔር በጎ ፈቃድ ሆኖአልና። ፩ ቆሮ ፩፣ ፳፩።
o ሰው ከተፈጠረ በኋላ የሚያውቀው እግዘአብሔር የፈጠረውን መልካም ብቻ ነበር፤ የተከለከለችውን -በተለምዶ ዕጸ-በለስ – ዛፍን ከበላ በኋላ ክፉንም አወቀ፤ ለዚህ ነው ዛፊቱ፡- «፣መልካምና ክፉን የምታሳውቅ ዛፍ» የተባለች። ከውድቀት በኋላ ሰው በተሰጠው አእምሮ በዘመናት ሁሉ እውቀቱን በማሳደጉ ወደ እነዚህ ሁለት ጎራዎች ሄዷል፡- ወደ መልካምና ወደ ክፉ።
§ መልካም ውጤት – ምድርን ለኑሮ አመቺ ማደረጋችን – መጓጓዣ፣ መኖሪያ…ማሻሻላችን.
§ ክፉ ውጤት – ሰው ሰራሽ የጥፋት ስጋቶች መፈጠራቸው፡- ጠመንጃ፣ መርዝ….መሥራታችን
ስለዚህ አዳም /ሰው/ መልካሙንና ክፉን የምታስታውቀውን ዛፍ ስለበላ እና ስላወቀ – ያወቀውን መተግበር ጀመር።
o የተሰጠን አእምሮ ዋናው ዓላማ በተፈጠርንበት መልካምነት፣ መልካም የሆነውን ፍጥረት በማስተዳደር ፣መልካም የሆነውን እግዚአብሔርን በመፈለግና /በመምረጥ/ ለማምለክ ነበረ።
o ፍለጋውን ማስቆም አይቻልም፤ ሰው ወደደም ጠላም በፍለጋ ውስጥ ነው።
ዓይን እስካለ አላይም ማለት አይቻልም፤ እግርም እስካለ አልሄድም ማለት አይቻልም።
o ፍለጋው ወደ እግዚአብሔር ሊያደርሰን ይችላል፣ ከእግዚአብሔር ሊያርቀንም ይችላል። እንደ ምንሄድበት አቅጣጫ ይወሰናል።
o ስለዚህ በሕይወት ጉዞ ላይ- በነገሮች ፍለጋ ዋናው ቁምነገር ዝምብሎ መሄዳችን /መኖራችን/ ሳይሆን ወዴት እየሄድን ነው? የሚለው ነው። ዋናው አቅጣጫው ነው።
ግን እግዚአብሔርን የምንፈልገው የት ነው?……. ይቀጥላል።
እግዚአብሔርን ማወቅ- ክፍል …..3…..
የእግዚአብሔር ባሕርያት
ስለእግዚአብሔር ለማወቅ ፍንጭ የሚሰጡን፣ የሚገልጡት ባሕርያቱ ናቸው።
መገለጫዎቹ፡-
፩. አይታይም፡- እግዚአብሔር ረቂቅ – መንፈስ ነው። ደቃቅ ሆኖ በአጉሊ መነጽር /በማይክሮስኮፕ/ ወይም ሩቅ ሆኖ በርቀት – መነጽር /በቴሌስኮፕ/ የሚታይ አይደለም።
– « ብቻውን አምላክ ለሚሆን ለማይጠፋው ለማይታየውም ለዘመናት ንጉሥ ምስጋናና ክብር እስከ ዘላለም ድረስ ይሁን፤ አሜን።» ፩ ጢሞ ፩፣ ፲፯
o በስሜት ሕዋሳቶቻችን ልንደርስበት አንችልም።
o ከምናውቃቸው በመጀመር የርቀት /የመርቀቅ/ ቅደም ተከተል ሲቀመጥ ፡ ከግዙፍ ወደ ረቂቅ፡-
o እግዚአብሔር የማይታይ እንጂ የማያይ አይደለም።
o በእምነት ግን በሕይወታችን እናየዋለን።
፪. አይወሰንም፡- በስፍራ/በቦታ የተወሰነ አይደለም። በዚያ አለ፤ በዚህ የለም፤ ይሄዳል/ይመጣል… አይባልም።
– «ከመንፈስህ ወዴት እሄዳለሁ? ከፊትህስ ወዴት እሸሻለሁ?
ወደ ሰማይ ብወጣ፥ አንተ በዚያ አለህ። ወደ ሲኦልም ብወርድ፥ በዚያ አለህ።
እንደ ንስር የንጋትን ክንፍ ብወስድ፥ እስከ ባሕር መጨረሻም ብበርር፥
በዚያ እጅህ ትመራኛለች፥ ቀኝህም ትይዘኛለች።» መዝ ፻፴፱/፻፵፣ ፯ – ፲
o በሁሉም ቦታ አለ። ይህ ሲባል ግን በየቦታው ያሉት ነገሮች ሁሉ ግን የእርሱ አካል ናቸው ማለት አይደለም።
፫. አይለወጥም፡- በጊዜ ተጽእኖ ሥር አይደለም። ሁሉም ነገሮች በጊዜ ብዛት ይለወጣሉ፣
– «…. ደግሞ። ጌታ ሆይ፥ አንተ ከጥንት ምድርን መሠረትህ፥ ሰማዮችም የእጆችህ ሥራ ናቸው፤ እነርሱም ይጠፋሉ አንተ ግን ጸንተህ ትኖራለህ፤ ሁሉም እንደ ልብስ ያረጃሉ፤ እንደ መጎናጸፊያም ትጠቀልላቸዋለህ ይለወጡማል፤ አንተ ግን አንተ ነህ፥ ዓመቶችህም ከቶ አያልቁም» ዕብ ፩፣ ፲ – ፲፪
o ጊዜ/ዘመን ሁሉንም ያስረጃል። እግዚአብሔር ግን ዘመንን ራሱን ያስረጀዋል።
o እግዚአብሔር ብሉየ-መዋዕል፡- የተባለው በግዕዝ – ዘመናትን የሚያስረጅ ማለት ነው።
o እግዚአብሔር የሚያልፍበት ወይም የሚጠብቀው ጊዜ የለም። ትናንት/ነገ – የዛሬ ዓመት የሚቀጥለው ዓመት.. የሚባል የለም። በእርሱ ዘንድ ሁልጊዜ ዛሬ ነው።
«ያለውና የነበረው የሚመጣውም ሁሉንም የሚገዛ ጌታ አምላክ። አልፋና ዖሜጋ እኔ ነኝ ይላል።» ራእ ፩፣ ፰
o ሰው ሊገዛ/ ሊቆጣጠር የሚችለው ያለውን /የአሁኑን/ ብቻ ነው። ለዚያውም የሚታየውን እና የቻለውን ያህል።
o እግዚአብሔር ግን ያለውን፡ የነበረውን/ያለፈውን/ የሚመጣውንም ሁሉ ይገዛል፤ ይቆጣጠራል፣ ያስተዳድራል።
o በእኛ ዘንድ ሺህ ዓመት በእግዚአብሔር ዘንድ እንደ አንድ ቀን ነው ሲባል እግዚአብሔር የሺ ዓመቱን ሥራ ዛሬ እንደተደረገ ያህል ነው – በዝርዝር የሚያውቀው። እኛ እንረሳለን።
o እግዚአብሔር ስለማይለወጥ ስለእርሱ በትክክል የገባን ነገር አይለወጥም። ያው ነው ማለት ነው። ስለእርሱ በእርግጠኝነት መናገር እንችላለን። እንዲህ ነው ብለን።
ስለ ሰው ግን እገሌ እንዲህ ነው ብለን በእርግጠኝነት መናገር አንችልም ፣ ሰው ይለወጣልና።
– እግዚአብሔር ስለማይለወጥ ዘላለማዊ ነው፣
o የነበረ፣ ያለ ፣ የሚኖር ነው። ለሙሴ እንደተናገረው። – እግዚአብሔርም ሙሴን፦ «ያለና የሚኖር» እኔ ነኝ አለው፤ ዘፍ ፫፣ ፲፬
፬. አይከፋፈልም፡ ሰው በሁለት ይከፈላል – ነፍስና ሥጋ ። ሰውነቱ/- ከአጥንት፣ ከደም፣ ከሥጋ የተሠራ ነው። ነፍሱ የእግዚአብሔር እስትንፋስ ሆና መንፈስ አለው፤
o እግዚአብሔር ግን ከዚህ እና ከዚህ ነገሮች የተዋቀረ/የተገኘ ነው አይባልም።
o እርሱ ሁሉን ያስገኘ እንጂ እርሱን የሚያስገኙ/ያስገኙ ነገሮች የሉም።
/ይቀጥላል/…
እግዚአብሔርን ማወቅ ….1…..
“….በሕይወትም ትኖራላችሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።” ሕዝ ፴፯፣፮
በሕይወት የመኖራችን ዓላማ እግዚአብሔርን ማወቅ ከሆነ እግዚአብሔርን እናውቀዋለን ወይ?
ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን፥ ከሚቃጠልም መሥዋዕት ይልቅ እግዚአብሔርን ማወቅ እወድዳለሁና። ሆሴዕ ፮፣ ፮
፩. እግዚአብሔርን ማወቅ ያለብን ለምንድን ነው?
– ለሕይወት ስኬት – ለምድራዊ አስቤዛ ኑሮ መሟላት?
– ከኑሮ ጭንቀት ለመላቀቅ – ሰላምና እረፍት ለማግኘት?
– ለጠቅላላ ዕውቀት/ለመረጃ? – አለ ወይስ የለም? እውነቱን ለማወቅ-
እግዚአብሔር ሲባል – ወደ አእምሮአችን / ወደ ምናባችን የሚመጣው ምስል ምንድን ነው?
o በሩቅ በሰማይ ያለ- ቁልቁል የሚያይ ሽማግሌ መሰል……?
o ወይም ሌላ ምስል…….?
እግዚአብሔርን ስናስብ ትዝ የሚለን ምንድን ነው?
– እግዚአብሔርን ወይስ ከእግዚአብሔር የሆኑ ነገሮችን፤
– እግዚአብሔር በሕይወታችን በኃይሉ እየሠራ ነው? ወይስ
በአእምሮአችን እንዲሁ የተቀመጠ ከብዙ ጉዳዮች መካከል አንዱ ነው?
– እግዚአብሔርን ነው ወይስ ስለእግዚአብሔር ነው የምናውቀው?
ስለጃንሆይ ልናውቅ እንችላለን፤ ጃንሆይን ግን ላናውቃቸው እንችላለን፤ አላየናቸውም፣ አላገኘናቸውምና።
– እግዚአብሔርን እናውቀዋለን? – እርሱስ ያውቀናል? – እንተዋወቃለን?
– እናናግረዋለን? – ከሆነስ — ይሰማናል? — ይመልስልናል? – እንደሚመልስልን ይሰማናል?
ከእነዚህ ጥያቄዎች አንዱ መልሳችን «አይ» ከሆነ – እግዚአብሔርን አላወቅነውም። ወይም ስለእግዚአብሔር ያወቅነው አልገባንም።
– እግዚአብሔር ሊታወቅ ይችላል? ወይስ አይችልም? –
የምታመልኩትን እየተመለከትሁ ሳልፍ። ለማይታወቅ አምላክ የሚል ጽሕፈት ያለበትን መሠዊያ ደግሞ አግኝቼአለሁና። እንግዲህ ይህን ሳታውቁ የምታመልኩትን እኔ እነግራችኋለሁ። የሐዋ ፲፯፣ ፳፫
እናንተስ ለማታውቁት ትሰግዳላችሁ፤ እኛ መዳን ከአይሁድ ነውና ለምናውቀው እንሰግዳለን። ዮሐ ፬፣፳፪
እግዚአብሔርን የምናመልከው አውቀነው ነው? ወይስ ባይገባንም ማምለክ ስላለብን? ወይስ እንዲሁ በዘልማድ ሌሎች ስላደረጉት?
እግዚአብሔርን ማወቅ/አለማወቅ ያለው ተጽእኖ
– በሕይወታችን ለነገሮች ቅድሚያ የምንሰጠው ካለን የእግዚአብሔርን እውቀት አንጻር ነው።
በደንብ ካወቅነው/ከገባን እንኖርለታለን። እንኖርበታለን። — ካልሆነ እንደ ትርፍ/ተጨማሪ እናየዋለን።
– በሕይወታችን በሚገጥሙን ፈተናና እና ችግሮች የምንወስዳቸው ውሳኔዎች እግዚአብሔርን ምን ያህል እንደምናውቀው ያሳያሉ።
– ሕይወትን ለመኖር የሚያስመኘው ስኬቶቻችን ናቸው – ወይስ በዓላማ መኖራችን?
የዚህ ዓለም ስኬት መጨረሻው ምንድን ነው?.. ምን ስናገኝ ነው በቃ የምንለው?
– በየዕለቱ/ በየጊዜው አእምሮአችን የሚይዘው ምንድን ነው? በልባችን እና በአእምሮአችን ሰፊውን ስፍራ የያዘው እግዚአብሔርን ከማወቅ / ካለማወቅ ጋር የሚያያዝ ነው።
አንድ ባለሃብት ለአንድ አገልጋይ ያለውን ሰፊ የልማት/ የእርሻ ቦታ ሲያስጎበኘው ከስፋቱ የተነሳ በአንድ ቀን ተጎብኝቶ ሊያልቅ አልቻለም። ኋላ ባለሃብቱ «እንዴት ነው? ምን ተሰማህ?» ብሎ የሙገሳ ቃል ሲጠብቅ አገልጋዩ፡ «ይህንን ሁሉ ሃብት ለማስተዳደር ልብህ በዚህ ስለሚጠመድ ያሳዝነኛል» አለው።
የዚህ ባለሃብት ልብ አሁን እየኖረበት ካለ ዓለም ጋር የተቆራኘ ነው።
ለአሁኑ እና ለዘላለሙ፣ ላለውና ለሚመጣው ነገር ሁሉ የምንሰጠው ዋጋ/ቦታ ባለን የእግዚአብሔር ዕውቀት ላይ የተመሠረተ ነው።
……………ይቀጥላል…………..
እግዚአብሄርን ማክበር ምንድነው ?
ክርስቲያን ሁሉ በህይወትህ የምትፈልገው አንድ ነገር ምንድነው ተብሎ ሲጠየቅ የሚመልሰው “እግዚአብሄርን ማክበር” የሚል ነው፡፡ ምንም እንኳን እግዚአብሄርን ማክበር የሚለው ንገግር ሰፊ ፣ ግልፅ ያልሆነና ተጨማሪ ማብራሪያ የሚያስፈልገው መልስ ቢሆንም ትክክለኛ መልስ ነው፡፡ የተሰራነውና የተፈጠርነው ለእግዚአብሄር ክብር ነው፡፡
በስሜ የተጠራውን ለክብሬም የፈጠርሁትን፥ የሠራሁትንና ያደረግሁትን ሁሉ አምጣ እለዋለሁ። ኢሳይያስ 43፡7
ሁላችንም ልባችን የሚቃጠልለት እግዚአብሄርን የማክበር አላማ ግን ምንድነው ? በህይወታችን የምንፈልገው ምንድነው? እግዚአብሄር ማክበራችንንና አለማክበራችንን እንዴት እናውቃለን? እግዚአብሄርን ማክበራችን እንዴት ይመዘናል? እግዚአብሄርን ማክበራችን እንዴት እናሳካዋለን፡፡ እግዚአብሄርን ማክበር በተግባር ምን ማድረግ ነው? እግዚአብሄርን ማክበራችን እንዴት ይለካል? የሚሉትን ጥያቄዎች መመለስ እግዚአብሄር የማክበር አላማችንን ለማሳካት እጅግ ይጠቅመናል፡፡
ለእግዚአብሄር ክብር መኖር ማለት
• ለሌሎች መልካምን ማድረግ ነው
በምናደርገው መልካምነት የእግዚአብሄርን መልካምነት ማሳየት ማንፀባረቅ ነው፡፡ ከምድራዊ ሰዎች የእንካ በእንካ አሰራር የተለየ ከእግዚአብሄር ብቻ የሚገኝን በሁኔታዎች ላይ ያልተደገፈ መልካምነት በመኖር ለሰዎች ወደ እግዚአብሄር ማመልከት ነው፡፡ ሰዎች የእኛን ኑሮ አይተው ይህ የሰው ስራ አይደለም ብለው እግዚአብሄርን ራሱን እንዲያመሰግኑት ማድረግ ነው፡፡ ለሁሉም ሰው መልካምነትን በማሳየት የእግዚአብሄርን ታላቅ ችሎታ ማሳየት ነው፡፡
መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ። ማቴዎስ 5፡16
እናንተ ግን ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃኑ የጠራችሁን የእርሱን በጎነት እንድትናገሩ የተመረጠ ትውልድ፥ የንጉሥ ካህናት፥ ቅዱስ ሕዝብ፥ ለርስቱ የተለየ ወገን ናችሁ፤ 1ኛ ጴጥሮስ 2፡9
• የእግዚአብሄርን ስም መሸከም ማለት ነው
የእግዚአብሄር ስም በመልካም ሁሉ እንዲነሳ ሰዎች በእኛ ህይወት የእግዚአብሄርን ፍቅር እንዲያዩ ማድረግ ነው፡፡ በእኛ ምክኒያት የእግዚአብሄር ስም በክፉ አንዳይነሳ መጠንቀቅ ነው፡፡ የእግዚአብሄር ስም ከፍ ብሎ እንዲታይ የሚያስፈልገውን መስዋእትነት ሁሉ መክፈል ነው፡፡ እግዚአብሄርን በሚገባ መወከል ማለት ነው፡፡
ጌታም፦ ይህ በአሕዛብም በነገሥታትም በእስራኤልም ልጆች ፊት ስሜን ይሸከም ዘንድ ለእኔ የተመረጠ ዕቃ ነውና ሂድ፤ ስለ ስሜ ስንት መከራ ሊቀበል እንዲያስፈልገው እኔ አመለክተዋለሁና አለው።ሐዋርያት 20፡15-16
• ቃሉን በመታዘዝ ፍሬ ማፍራት ነው
ጌታን የምናከብርበትን መመሪያ የእግዚአብሄርን ቃል በመስማትና በመታዘዝ በዚያም ፍሬ በማፍራት ለእግዚአብሄርን ያለንን ፍቅርና አክብሮት ማሳየት ነው፡፡
በእኔ ብትኖሩ ቃሎቼም በእናንተ ቢኖሩ የምትወዱትን ሁሉ ለምኑ ይሆንላችሁማል። ብዙ ፍሬ ብታፈሩና ደቀ መዛሙርቴ ብትሆኑ በዚህ አባቴ ይከበራል። ዮሐንስ 15፡7-8
• ሃጢያትን መፀየፍ ከክፋት መሸሽ ነው፡፡
እግዚአብሄርን ማክበር ሃጢያትን በመፀየፍና በመሸሽ ቅዱስ የሆነውን እግዚአብሄርን በመምሰል ለቅዱሳን እንደሚገባ መኖር ነው፡፡ እግዚአብሄርን ማክበር ስጋችንን ሃጢያት በመከልከል እግዚአብሄርን ደስ ማሰኘት ነው፡፡
ለቅዱሳን እንደሚገባ ግን ዝሙትና ርኵሰት ሁሉ ወይም መመኘት በእናንተ ዘንድ ከቶ አይሰማ፤ ኤፌሶን 5፥3
ወይስ ሥጋችሁ ከእግዚአብሔር የተቀበላችሁት በእናንተ የሚኖረው የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደ ሆነ አታውቁምን? በዋጋ ተገዝታችኋልና ለራሳችሁ አይደላችሁም፤ ስለዚህ በሥጋችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ። 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ 6፡19-20
• የእግዚአብሄርን ፍላጎት መፈፀም ማለት ነው
ከፍላጎታችን በላይ የእግዚአብሄርን ፍላጎት ማሟላት ፣ የእኛን ፍላጎት ወደጎን በማድረግ የእርሱን ፍላጎት ማስቀደም ነው፡፡ የእግዚአብሄርን ፈቃድ ለማድረግ ራሳችንን መስጠት ማለት ነው፡፡ ከምንም ስሜታችን በላይ እግዚአበሄርን ለማስደሰት ቅድሚያ መስጠት ነው፡፡
ብትፈቅድ ይህችን ጽዋ ከእኔ ውሰድ፤ ነገር ግን የእኔ ፈቃድ አይሁን የአንተ እንጂ እያለ ይጸልይ ነበር። ሉቃስ 22፡42
• እግዚአብሄርን ብቻ መፍራት ማለት ነው
እንድንፈራቸው የሚፈልጉ በጣም ብዙ ነገሮች ባሉበት አለም ውስጥ እግዚአብሄርን ብቻ መፍራት ፣ እግዚአብሄርን ከሌሎች ጌቶች ጋር አለመቀላቀል ፣ ብቻውን መያዝና በህይወታችን የመጀመሪያውን ስፍራ መስጠት እግዚአብሄርን ከፍ ማድረግ ነው፡፡
ማስፈራራታቸውንም አትፍሩ አትናወጡም፥ ዳሩ ግን ጌታን እርሱም ክርስቶስ በልባችሁ ቀድሱት። 1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 3፡14-15
• እግዚአብሄርን ማመን ማለት ነው
በአካባቢያችን ያሉትን ነገሮች ባለማየት የማይታየውን እግዚአብሄርን በቃሉ ማመንና መታዘዝ ነው፡፡ ይህ በተፈጥሮ አይን የማይታየውን እግዚአብሄር በእኛ እንዲታይና እንዲከበር ያደርገዋል፡፡
እንግዲህ ሁልጊዜ ታምነን፥ በእምነት እንጂ በማየት አንመላለስምና በሥጋ ስናድር ከጌታ ተለይተን በስደት እንዳለን የምናውቅ ከሆንን፥ 2ኛ ቆሮንቶስ 5፡6-7
• ገንዘብን አለመውደድ ነው
ገንዘብን ሁሉንም ነገር ሊገዛ እንደማይችል በጣም ውስን እንደሆነ መረዳታችን ፣ መኖሪያችን እግዚአብሄር እንጂ ገንዘብ እናዳይደለ ማወቃችን ፣ ከገንዘብ ይልቅ ወደጌታ መጠጋታችንና ገንዘብን መናቃችን እግዚአብሄርን ያከብረዋል፡፡
ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚቻለው ማንም የለም፤ ወይም አንዱን ይጠላል ሁለተኛውንም ይወዳል፤ ወይም ወደ አንዱ ይጠጋል ሁለተኛውንም ይንቃል፤ ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም። ማቴዎስ 6፡24
• የነፍሳችንን ጥያቄ መርሳት ነው
ነፍሳችን ብዙ ጥያቄ አላት ፡፡ ጥያቄዋን ሁሉ ከሰማንና ከቃሉ በላይ ካከበርናት እግዚአብሄርን አናከብረውም፡፡ እግዚአብሄርን ለማክበር የነፍሳችንን ጥያቄና ጩኸት መርሳት ይጠይቃል፡፡ ከነፍሳችን በላይ ቃሉን መስማትና መታዘዝ እግዚአብሄርን በህይወታችን ያከብረዋል፡፡
የእግዚአብሄርን ነገር አክብዶ ለመያዝ የራስን ነገር ቀለል አድርጎ መያዝ ይጠይቃል፡፡ ለእግዚአብሄር ስራ ቅድሚያ ለመስጠት የነፍሳችንን ጥያቄ አለመስማትና ቸል ማለት ይኖርብናል፡፡
ነፍሱን ሊያድን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታልና፤ ስለ እኔ ነፍሱን የሚያጠፋ ሁሉ ግን እርሱ ያድናታል። ሉቃስ 9፡24
ነገር ግን ሩጫዬንና ከጌታ ከኢየሱስ የተቀበልሁትን አገልግሎት እርሱም የእግዚአብሔርን ጸጋ ወንጌልን መመስከር እፈጽም ዘንድ ነፍሴን በእኔ ዘንድ እንደማትከብር እንደ ከንቱ ነገር እቆጥራለሁ። ሐዋርያት 20፥24
ሰውን በክርስቶስ ማወቅ
ስለዚህ እኛ ከአሁን ጀምሮ ማንንም በሥጋ እንደሚሆን አናውቅም፤ ክርስቶስንም በሥጋ እንደ ሆነ ያወቅነው ብንሆን እንኳ፥ አሁን ግን ከእንግዲህ ወዲህ እንደዚህ አናውቀውም። 2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 5፡16
ሰው የሚያይበትና እግዚአብሄር የሚያይበት አስተያየት ይለያያል፡፡
እግዚአብሔር ግን ሳሙኤልን፦ ፊቱን የቁመቱንም ዘለግታ አትይ፤ ሰው እንዲያይ እግዚአብሔር አያይምና ናቅሁት፤ ሰው ፊትን ያያል፥ እግዚአብሔር ግን ልብን ያያል አለው። መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 16፡7
የሰውን እውነተኛ ማንነት ሊነግረን የሚችለው የፈጠረው እግዚአብሄር ብቻ ነው፡፡ ሰው ስለሰው ማንነት ቢነግረን ሊሳሳት ይችላል፡፡
ሰውን በክርስቶስ ማየት ማለት ሰውን እግዚአብሄር እንደሚያየው ማየት ማለት ነው፡፡ እግዚአብሄር እንደሚያየው ካላየ በስተቀር ሰው ሰውን በትክክል ሊረዳው አይችልም፡፡ እግዚአብሄር እንደሚያየው ካላየ በስተቀር ሰው ከሰው ጋር በትክክል ህብረት ሊያደርግ አይችልም፡፡
ሰውን በሥጋ እንደሚሆን አናውቅም ሰውን የምናውቅው በክርስቶስ ነው ማለት ምንድነው?
• ሰውን በክርስቶስ እንጂ በስጋ እንደሚሆን አላውቀውም ማለት ክርስትያንን እግዚአብሄር እንደሚወደው እንጂ ሰው እንደሚያየው አላየውም፡፡
ሰው በሰው ላይ ብዙ አቃቂር ሊያወጣ ይችላል፡፡ ሰው እንኳን በሰው ላይ በራሱ ላይ እንኳን እንከን ያገኛል፡፡ የሰው ፍርድ ትክክል የማይሆነው ሰው አይኑ እንዳየ ጆሮው እንደሰማ ከፈረደ ነው፡፡ የሰው ፍርድ ትክክል የሚሆነው ሰው እግዚአብሄር አንደሚያየው አይቶ በፅድቅ ከፈረደ ነው፡፡ በፅድቅ መፍረድ ማለትደግሞ እግዚአብሄር እንደሚያየው አይቶ መፍረድ ማለት ነው፡፡
ቅን ፍርድ ፍረዱ እንጂ በመልክ አትፍረዱ። የዮሐንስ ወንጌል 7፡24
• ሰውን በክርስቶስ እንጂ በስጋ እንደሚሆን አላውቀውም ማለት ክርስትያን በክርስቶስ በመሆኑ ያለውን ቦታ እንጂ ሌሎች ነገሮችን አላይም ማለት ነው
ክርስትያን በእግዚአብሄር ቤተሰብ ውስጥ ባለው ቦታ እንጂ በስሜታችን ልናየው አይገባም፡፡ ክርስትያን በእግዚአብሄር መንግስት ባለው ቦታ ብቻ ክብር አለው፡፡ ክርስትያን ቦታው የሚጠይቀውን ክብር ማግኘት አለበት፡፡
ለሁሉ የሚገባውን አስረክቡ፤ ግብር ለሚገባው ግብርን፥ ቀረጥ ለሚገባው ቀረጥን፥ መፈራት ለሚገባው መፈራትን፥ ክብር ለሚገባው ክብርን ስጡ። ወደ ሮሜ ሰዎች 13፡7
• ሰውን በክርስቶስ እንጂ በስጋ እንደሚሆን አላውቀውም ማለት ክርስቲያን በክርስቶስ ባለው እምቅ ሃይል እንጂ በውጭ በሚታየው ድካም አላየውም፡፡
ክርስትያን የእግዚአብሄር ልጅ ነው፡፡ ቢደክም ድካሙን የሚሸፍን የእግዚአብሄር ፀጋ ተገልጦዋል፡፡ ስለዚህ ድካምን ብቻ አይቶ የሚያበረታውን ፀጋ አለማየት ፍርዳችንን ፍርደ ገምድል ያደረገዋል፡፡
እርሱም፦ ጸጋዬ ይበቃሃል፥ ኃይሌ በድካም ይፈጸማልና አለኝ። እንግዲህ የክርስቶስ ኃይል ያድርብኝ ዘንድ በብዙ ደስታ በድካሜ ልመካ እወዳለሁ። ስለዚህ ስለ ክርስቶስ በድካም በመንገላታትም በችግርም በስደትም በጭንቀትም ደስ ይለኛል፤ ስደክም ያን ጊዜ ኃይለኛ ነኝና። 2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 12፡9-10
• ሰውን በክርስቶስ እንጂ በስጋ እንደሚሆን አላውቀውም ማለት ሰውን በስጋ ያሉትን ነገሮች አልቆጥራቸውም
ሰውን በክርስቶስ እንጂ በስጋ እንደሚሆን አላውቀውም ማለት ሰውን ዘሩን አላይም፣ ተፈጥሮአዊ ድካሙን አላይም ፣ ፆታውን አላይም የመጣበትን የኋላ ታሪክ አላይም ማለት ነው፡፡
አለቆች የመሰሉት ግን፥ በፊት ማን እንደ ነበሩ አይገደኝም፤ እግዚአብሔር የሰውን ፊት አይቶ አያደላም፤ አለቆች የመሰሉት አንዳች እንኳ አልጨመሩልኝምና፥ ወደ ገላትያ ሰዎች 2፡6
• ሰውን በክርስቶስ እንጂ በስጋ እንደሚሆን አላውቀውም ማለት ሰውን እግዚአብሄር እንደሚያየው እንጂ ሰው እንደሚያየው አላየውም፡፡
• ሰውን በክርስቶስ እንጂ በስጋ እንደሚሆን አላውቀውም ማለት እግዚአብሄር ሰዎችን ለመገሰፅ ካልተጠቀመብን በስተቀር በራሳችን አነሳሽነት ብቻ በሰዎች ላይ እንፈርድም ማለት ነው፡፡
ነገር ግን በእናንተ ዘንድ ወይም በሌላ ሰው ዘንድ ብፈረድ ለእኔ ምንም አይደለም፤ እኔም በራሴ እንኳ አልፈርድም፤ 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 4፡3
• ሰውን በክርስቶስ እንጂ በስጋ እንደሚሆን አላውቀውም ማለት ሰውን በክቡር ደሙ እንደተዋጀ ክቡር ፍጥረት እንጂ እንደተራ ሰው አላየውም ማለት ነው፡፡
ከአባቶቻችሁ ከወረሳችሁት ከከንቱ ኑሮአችሁ በሚያልፍ ነገር በብር ወይም በወርቅ ሳይሆን፥ ነውርና እድፍ እንደ ሌለው እንደ በግ ደም በክቡር የክርስቶስ ደም እንደ ተዋጃችሁ ታውቃላችሁ። 1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 1፡18-19
ስለዚህ እኛ ከአሁን ጀምሮ ማንንም በሥጋ እንደሚሆን አናውቅም፤ ክርስቶስንም በሥጋ እንደ ሆነ ያወቅነው ብንሆን እንኳ፥ አሁን ግን ከእንግዲህ ወዲህ እንደዚህ አናውቀውም። 2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 5፡16
የየዋህነት ክብር
የዋህነት የመንፈስ ፍሬ እንደሆነና መንፈሳዊ ውጤታችንና ፍሬያማነታችነ የሚለካበት ወሳኝ ባህሪ እንደሆነ መፅሃፍ ቅዱስ ያስተምራል፡፡
የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፥ ደስታ፥ ሰላም፥ ትዕግሥት፥ ቸርነት፥ በጎነት፥ እምነት፥ የውሃት፥ ራስን መግዛት ነው። ገላትያ 5፡22
በነገር ሁሉ ምሳሌያችን የሆነው ኢየሱስ የዋህ ነበረ፡፡ ከእኔም ተማሩ ብሎ ያስተምረናል፡፡
ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ፥ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፥ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ ማቴዎስ 11፡29
የዋህነት የጥሪያችን ደረጃ ነው፡፡ ከየዋህነት ያነሰ ኑሮ እንድንኖር አልተጠራንም፡፡ ለጥሪያችን እንደሚገባ መኖር በየዋህነት መኖር ነው፡፡
እንግዲህ በጌታ እስር የሆንሁ እኔ በተጠራችሁበት መጠራታችሁ እንደሚገባ ትመላለሱ ዘንድ እለምናችኋለሁ፤ በትሕትና ሁሉና በየዋህነትበትዕግሥትም፤ እርስ በርሳችሁ በፍቅር ታገሡ፤ ኤፌሶን 4፡1-2
ስለየዋህነት መፅሃፍ ቅዱስ ብዙ ያስተምራል፡፡ ለምሳሌ ያህል ይህን ያህል ስለ የዋህነት አስፈላጊነት ካየን የየዋህነትን ትርጉም እንመልከት፡፡
ግን የዋህነት ምንድነው?
የዋህነት በብዙ ቃላት ሊተረጎም የሚችል ቃል ነው፡፡ የየዋህነትን ትርጉም እንመልከት፡-
ቸር
መልካምና ርህሩህ አዛኝ ስለሌላው ግድ የሚለው
ክፉና ግፈኛ ያልሆነ
ለሰው የሚጠነቀቅ ፣ ግዴለሽ ያልሆነ ፣ ራስ ወዳድ ያልሆነ ፣ የሰውን ፍላጎት የሚያከብር
ልከኛ
ለጥቅም የማይስገበገብ ፣ በቃኝ የሚል ፣ ለመኖር ብዙ ነገር የማይጠይቅ
የተከበረ
ሰዎች የሚያከብሩት ፣ ክብሩን ጠብቆ የሚኖር ፣ የሚያዋርደውንና የሚያስንቀውን ክፉ ነገር የማያደርግ
ጨዋ
የተገራ ፣ ለጥቅም የማይጣላ ፣ በራስ ወዳድነት የማይከራከር
ሰላማዊ
ሰላም ያለው ፣ ለሌላም ሰላም የሚሰጥ ፣ አስጊ ያልሆነ
አክባሪ
ሰውን አክባሪ ፣ ሰውን የማይንቅ ፣ ለሰው ትልቅ ስፍራ ያለው
ጭምት
ረጋ ያለ ፣ የማይቸኩል ፣ ቁጥብ ፣ ስሜቱን የሚገዛ
በተራ ነገር ላይ የማይገኝ
በትክክለኛው መንገድ የማይመጣን ጥቅም የሚንቅ ፣ ነውረኛ ረብ የማይወድ
ደረጃው ከፍ ያለ
መልካም ባህሪ ያለው በሚሉት ቃላት ሊገለፅ ይችላል፡፡
እኛ የምንሰራው ከፍ ላለ ነገር ነው፡፡እኛ የምንሰራው ለመንግስቱ ነው፡፡ እኛ የምንፈልገው የእግዚአብሄርን ፅድቅ ነው፡፡ ሌላ ሁሉ በእግዚአብሄር የሚጨመርልን የእግዚአብሄር ቤተሰብ አባላት ነን፡፡
እግዚአብሔር የሚለውን እንስማ
እግዚአብሄር ደግሞ አንዳንዴ ሳይሆን ሁል ጊዜ ይናገራል፡፡ እግዚአብሄር በስራ ላይ ነው፡፡ እግዚአብሄር ሁል ጊዜ እየተናገረ ነው፡፡ የእኛ ሃላፊነት እግዚአብሄርን እንዲናገረን ማድረግ ሳይሆን እግዚአብሄርን መስማት ነው፡፡ የእኛ ሃላፊነት የእግዚአብሄርን ፈቃድ እንዴት እንደምንረዳ ማወቅ ነው፡፡
ብዙ ጊዜ ሰዎች እግዚአብሄርን የማይሰሙት እግዚአብሄር ስላልተናገረ ወይም እግዚአብሄር ፈቃድ ፈቃዱን ሰውሮት ሳይሆን እግዚአብሄር እንዲናገራቸው የሚጠብቁት በጣም አስደናቂና ድራማዊ መንገድ ስለሆነ ነው፡፡
ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ እግዚአብሄር የሚናገር የሚመስላቸው በነጎድጉዋድ ድምፅ ከሰማይ በከፍተኛ ድምፅ ነው፡፡ እውነት ነው እግዚአብሄር እንደዚያም ይናገራል፡፡ ነገር ግን እግዚአብሄር እጅግ ለተለየ ሁኔታ ካልሆነ በስተቀር በዚያ መልክ አይናገርም፡፡
ኤልያስ እግዚአብሄርን በነፋስ ፣ በምድር መናወጥ እንዲሁም በእሳት ውስጥ ቢጠብቀውም እግዚአብሄር ግን ሰዎች በሚጠብቁዋቸው በነጎድጉዋድ ውስጥ አልነበረም፡፡
እርሱም፦ ውጣ፥ በተራራውም ላይ በእግዚአብሔር ፊት ቁም አለ። እነሆም፥ እግዚአብሔር አለፈ፥ በእግዚአብሔርም ፊት ትልቅና ብርቱ ነፋስ ተራሮቹን ሰነጠቀ፤ ዓለቶቹንም ሰባበረ፥ እግዚአብሔር ግን በነፋሱ ውስጥ አልነበረም። ከነፋሱም በኋላ የምድር መናወጥ ሆነ፥ እግዚአብሔር ግን በምድር መናወጥ ውስጥ አልነበረም። ከምድር መናወጥ በኋላ እሳት ሆነ፥ እግዚአብሔር ግን በእሳቱ ውስጥ አልነበረም። ከእሳቱም በኋላ ትንሽ የዝምታ ድምፅ ሆነ። 1ኛ ነገሥት 19፡11-12
መንፈሳችን የእግዚአብሄርን ፈቃድ ያውቃል፡፡ ከእግዚአብሄር ዳግም በተወለደው በመንፈሳችን ውስጥ የእግዚአብሄር ፈቃድ አለ፡፡ የእኛ ሃላፊነት ያንን የእግዚአብሄርን ፈቃድ ለመረዳት ጊዜ ወስደንም ልባችንን መስማት ነው፡፡ የእኛ ሃላፊነት ጊዜ ወስደን የመንፈስን ምስክርነት በልባችን ውስጥ መፈለግና መስማት ነው፡፡ የእግዚአብሄን ፈቃድ ለመስማት ራሳችንን ስንሰጥ ትንሽዋን የለሆሳስ ድምፅ በልባችን መስማት እንችላለን፡፡
በእግዚአብሔር መንፈስ የሚመሩ ሁሉ እነዚህ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸውና። የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ያ መንፈስ ራሱ ከመንፈሳችን ጋር ይመሰክራል። ሮሜ 8፡14፣16
የእግዚአብሄርን ፈቃድ እንድናውቅ ተሰጥቶናል፡፡ ይህንን የእግዚአብሄርን ፈቃድ የምናውቀው በመንፈሳችን አማካኝነት ነው፡፡ ይህ በስንት ጊዜ አንድ ጊዜ የሚሆን ሳይሆን መንፈሳችን በሰማን ቁጥር የእግዚአብሄርን ፈቃድ የምንሰማበት መንገድ ነው፡፡
በእርሱ ውስጥ ካለው ከሰው መንፈስ በቀር ለሰው ያለውን የሚያውቅ ሰው ማን ነው? እንዲሁም ደግሞ ከእግዚአብሔር መንፈስ በቀር ለእግዚአብሔር ያለውን ማንም አያውቅም። እኛ ግን ከእግዚአብሔር እንዲያው የተሰጠንን እናውቅ ዘንድ ከእግዚአብሔር የሆነውን መንፈስ እንጂ የዓለምን መንፈስ አልተቀበልንም። 1ኛ ቆሮንቶስ 2፡11-12
ስለ አንድ ነገር የእግዚአብሄርን ፈቃድ ማወቅ ስንፈልግ ልባችንን መስማት ያስፈልገናል፡፡ በልባችን የእግዚአብሄን አዎንታ ወይም አሉታ ምልክት እንፈልጋለን፡፡ በልባችን የእግዚአብሄርን የፈገግታ ወይም የተኮሳተረ ፊት እንፈልጋለን፡፡ የእግዚአብሄርን ፈቃድ ማወቅ ስንፈልግ በልባችን መንፈሳዊውን የማስጠንቀቂያ ቀይ መብራት ወይም የይለፍ አረንጋዴ መብራት ለመለየት ጊዜ መውሰድ ያስፈልገናል፡፡
የእግዚአብሄርን ፈቃድ ማወቅ ስንፈልግ በልባችን መንፈሳዊውን የማስጠንቀቂያ ቀይ መብራት ወይም የይለፍ አረንጋዴ መብራት ለመለየት ለመለየት ጊዜ መውሰድ ያስፈልገናል፡፡
የእግዚአብሄርን ፈቃድ ለማወቅ ስለምንፈልግበት ነገር ስናስብ እና በፀሎት ልባችንን ለመስማት ጊዜ ስንወስድ ልባችን ወይ በሰላም ይሞላል ወይም ልባችን ይረበሻል፡፡ ለእግዚአብሄ ፈቃድ ልባችንን ስናዳምጥ ወይ ልባችን በደስታ ይሞላል ወይም ይኮሰኩሰናል፡፡ ስለዚህ ነው ለልባችን ሰላም ቅድሚያ መስጠትና በልባችን ሰላም ካልተሰማን የእግዚአብሄር ፈቃድ ስላይደለ ማድረግ የሌለብን፡፡ በልባችን ደሰታ ከፈሰሰና ሰላም ከተሰማን ደግሞ የእግዚአብሄር ፈቃድ መሆኑን አውቀን ማድረግ ያለብን፡፡
በአንድ አካልም የተጠራችሁለት ደግሞ የክርስቶስ ሰላም በልባችሁ ይግዛ፤ ቆላስይስ 3፡15
መዝገብህ ባለበት ልብህ
ልብህ የሚሄደው መዝገብህ ባለበት ቦታ ነው፡፡ ሰው በተፈጥሮው ሃብቱና ልቡ ተነጣጠለው አይኖሩም፡፡ መዝገብህ ባለበት ልብህ በዚያ ይሆናል፡፡
መዝገብህ በሌለበት ቦታ ልብህ በዚያ አይኖርም፡፡ ትኩረትህ ሁሉ የሚኖረው የኔ የምትለው የምትጠነቀቅለት ነገር ባለበት ቦታ ነው፡፡ ስለዚህ አለ ኢየሱስ ልባችሁ በሰማይ እንዲያተኩር ወሳኙ መንገድ ፣ ልባችሁ በሰማይ እንዲቀር የሚረዳው ነገር ፣ ልባችሁ በሰማይ ትኩረት እንዲያዝ ከፈለጋችሁ መዝገባችሁን በሰማይ አስቀምጡ እያለን ነው፡፡
በምድር ላይ የምንደገፍበት ነገር ሲጠፋ ልባችን ወደ ሰማይ መዝገብ ያዘነብላል፡፡ ነገር ግን የምድር ሃብታችን ሲበዛና በዚያም ለመታመን ስንፈተን ልባችንም በምድር ላይ ይቀራል፡፡ ልባችንን የምንጥልበት ሃብታችን በምድር ላይ እየበዛ በሄደ መጠን ልባችን ከሰማይ ላይ እየተነሳ ይሄዳል፡፡ መዝገባችን በምድር ሲሆን ልባችንም በምድር ይሆናል፡፡ መዝገባችን በሰማይ ሲሆን በቅፅበት ልባችንም በሰማይ ይሆናል፡፡
ብዙ ጊዜ ልባችን ከሰማይ በመነሳት እንፈተናልን፡፡ በዚህ ፈተና ያለመውደቅ መንገዱን ኢየሱስ ያስተምራል፡፡ መዝገብን በምድር የመሰብሰብ ጉዳቱ ልባችንን ከሰማይ ላይ እንዲነሳ ሰማይ ትኩረታችን እንዳይሆን ያደርጋል፡፡ መዝገብን በሰማይ የመሰብሰብ ጥቅሙ ልባችንን በሰማይ ይሰበስብልናል፡፡
ብልና ዝገት በሚያጠፉት ሌቦችም ቆፍረው በሚሠርቁት ዘንድ ለእናንተ በምድር ላይ መዝገብ አትሰብስቡ፤ ነገር ግን ብልም ዝገትም በማያጠፉት ሌቦችም ቆፍረው በማይሠርቁት ዘንድ ለእናንተ በሰማይ መዝገብ ሰብስቡ፤ መዝገብህ ባለበት ልብህ ደግሞ በዚያ ይሆናልና። ማቴዎስ 6፡19-21
ሰማይ በጨረፍታ
10-11 በመንፈስም ወደ ታላቅና ወደ ረጅም ተራራ ወሰደኝ፥ የእግዚአብሔርም ክብር ያለባትን ቅድስቲቱን ከተማ ኢየሩሳሌምን ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስትወርድ አሳየኝ፤ ብርሃንዋም እጅግ እንደ ከበረ ድንጋይ እንደ ኢያሰጲድ ድንጋይ ሆኖ እንደ ብርሌ የጠራ ነበረ፤
12 ታላቅና ረጅም ቅጥር ነበራት፥ አሥራ ሁለትም ደጆች ነበሩአት በደጆቹም አሥራ ሁለት መላእክት ቆሙ፥ የአሥራ ሁለቱም የእስራኤል ልጆች ነገዶች ስሞች ተጽፈውባቸው ነበር።
13 በምሥራቅ ሦስት ደጆች፥ በሰሜንም ሦስት ደጆች፥ በደቡብም ሦስት ደጆች፥ በምዕራብም ሦስት ደጆች ነበሩ።
14 ለከተማይቱም ቅጥር አሥራ ሁለት መሠረቶች ነበሩአት፥ በእነርሱም ውስጥ የአሥራ ሁለቱ የበጉ ሐዋርያት ስሞች ተጽፈው ነበር።
15 የተናገረኝም ከተማይቱንና ደጆችዋን ቅጥርዋንም ይለካ ዘንድ የወርቅ ዘንግ ነበረው።
16 ከተማይቱም አራት ማዕዘን ነበራት፥ ርዝመትዋም እንደ ስፋትዋ ልክ ነበረ። ከተማይቱንም በዘንግ ለካት አሥራ ሁለትም ሺህ ምዕራፍ ሆነች፤ ርዝመትዋና ስፋትዋ ከፍታዋም ትክክል ነው።
17 ቅጥርዋንም ለካ፥ መቶ አርባ አራት ክንድ በሰው ልክ፥ እርሱም በመልአክ ልክ።
18 ቅጥርዋም ከኢያሰጲድ የተሠራ ነበረ፥ ከተማይቱም ጥሩ ብርጭቆ የሚመስል ጥሩ ወርቅ ነበረች።
19 የከተማይቱም ቅጥር መሠረት በከበረ ድንጋይ ሁሉ ተጌጦ ነበር፤ ፊተኛው መሠረት ኢያሰጲድ፥ ሁለተኛው ሰንፔር፥ ሦስተኛው ኬልቄዶን፥ አራተኛው መረግድ፥
20 አምስተኛው ሰርዶንክስ፥ ስድስተኛው ሰርድዮን፥ ሰባተኛው ክርስቲሎቤ፥ ስምንተኛው ቢረሌ፥ ዘጠነኛው ወራውሬ፥ አሥረኛው ክርስጵራስስ፥ አሥራ አንደኛው ያክንት፥ አሥራ ሁለተኛው አሜቴስጢኖስ ነበረ።
21 አሥራ ሁለቱም ደጆች አሥራ ሁለት ዕንቆች ነበሩ፤ እየአንዳንዱ ደጅ ከአንድ ዕንቍ የተሠራ ነበረ። የከተማይቱም አደባባይ ጥሩ ብርጭቆ የሚመስል ጥሩ ወርቅ ነበረ።
22 ሁሉንም የሚገዛ ጌታ አምላክና በጉ መቅደስዋ ናቸውና መቅደስ በእርስዋ ዘንድ አላየሁም።
23 ለከተማይቱም የእግዚአብሔር ክብር ስለሚያበራላት መብራትዋም በጉ ስለ ሆነ፥ ፀሐይ ወይም ጨረቃ እንዲያበሩላት አያስፈልጓትም ነበር።
24 አሕዛብም በብርሃንዋ ይመላለሳሉ፥ የምድርም ነገሥታት ክብራቸውን ወደ እርስዋ ያመጣሉ፤
25 በዚያም ሌሊት ስለሌለ ደጆችዋ በቀን ከቶ አይዘጉም፥
26 የአሕዛብንም ግርማና ክብር ወደ እርስዋ ያመጣሉ።
27 ለበጉም በሆነው በሕይወት መጽሐፍ ከተጻፉት በቀር፥ ጸያፍ ነገር ሁሉ ርኵሰትና ውሸትም የሚያደርግ ወደ እርስዋ ከቶ አይገባም።
ራእይ 21፡10-27
ጊዜው አሁን ነው!
ጥበብን የተሞላ ልብ ይኖረን ዘንድ ፣ እድሜያችንን መቍጠር አስተምረን፡፡ መዝሙር 90፡12
በምድር ያለን ጊዜ ምን ያህል አጭር እንደሆነ በተረዳን መጠን ጊዜያችንን በአግባቡ ለመጠቀም እንተጋለን፡፡ የምድር ኑሮዋችን አጭር መሆኑን እስካላስታወስን ግን በተለያዩ ምክኒያቶች የምናባክነው ይበዛል፡፡
አቤቱ፥ ፍጻሜዬን አስታውቀኝ፥ የዘመኔ ቍጥሮች ምን ያህል እንደ ሆኑ፥ እኔ ምን ያህል ወደ ኋላ እንደምቀር አውቅ ዘንድ። መዝሙር 39፡4
በምድር ላይ ያለን ጊዜ የተሰጠንን ስራ ለመጨረስ የሚበቃ እንጂ ምንም የሚባክን ትርፍ ጊዜ የለንም፡፡ በጊዜ አስተዳደራችን እጅግ የተሳካልን ብንሆን ጊዜያችንን ሙሉ ለሙሉ ብንጠቀምበት ነው፡፡ የልባችንም ጩኸት በምድር ላይ ምን ያህል እንደምንኖር ማወቅ ነው፡፡ መፅሃፍ ቅዱስ በምድር ለይ የምንኖረው ለአጭር ጊዜ እንደሆነ ይናገራል፡፡
ሰው ከንቱን ነገር ይመስላል፤ ዘመኑ እንደ ጥላ ያልፋል። መዝሙር 144፡4
ሕይወታችሁ ምንድር ነው? ጥቂት ጊዜ ታይቶ ኋላ እንደሚጠፋ እንፍዋለት ናችሁና። ያዕቆብ 4፡14
እርግጥ ነው እግዚአብሄር በምድር ያለን ጊዜ አጭር እንደሆነ ይነግረናል እንጂ የሚቀረንን ቀን ምን ያህል እንደሆነ ቁጥሩን አይነግረም፡፡
እኛም የሚያስፈፈልገን ነገር ዛሬ ብቻ የእኛ እንደሆነና ዛሬን በሚገባ መጠቀም እንዳለብን ማወቅ ነው፡፡ ዛሬን በሚገባ እስከተጠቀምንበት ድረስ ህይወታችንን ሁሉ በሚገባ እንጠቀምበታለን፡፡
በዛሬ ስኬታማ ከሆንን በህይወት ዘመናችን ሁሉ ስኬታማ እንሆናለን፡፡ አንዳንዴ ነገ ለጌታ ለመኖር ልዩና የተሻለ እድል ይዞልን እንደሚመጣ እናስባለን፡፡እንደዚያ በማሰብ በዛሬ ላይ ካለአግባብ እንዝናናለን፡፡ ነገ ግን ምን እንደሚያመጣ አናውቅም፡፡ ነገ ካሰብነው በላይ ተግዳሮቶችን ይዞ ሊመጣ ይችላል፡፡ ዛሬንም ነገንም በሚረዳን በእግዚአብሄር እንጂ በነገ መመካት የለብንም፡፡
. . . ነገ የሚሆነውን አታውቁምና። ያዕቆብ 4፡13
ቀን የሚያመጣውን ምን እንደ ሆነ አታውቅምና ነገ በሚሆነው አትመካ። ምሳሌ 27፡1
መፅሃፍ ቅዱስ በግልፅ የምድር ጊዜያችን አጭር እንደሆነ ደጋግሞ ይነግረናል፡፡ በከንቱ የምንዝናናበትና የምናባክነው ትርፍ ጊዜ ጊዜ የለንም፡፡ ተርፎን የምናባክነው ምንም ጊዜ የለም፡፡
አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ነገን ወደዛሬ አምጥተንም መኖር እንፈልጋለን፡፡ እግዚአብሄር ቀኑን ጊዜውን እንደከፋፈለው ሁሉ በህይወት ያሉትን ስራዎቻችንን በጊዜ ከፋፍሎዋቸዋል፡፡ ነገን ዛሬ ላይ አምጥተን ለመኖር መሞከር ጥበብ አይደለም፡፡ የነገን ተግዳሮት ዛሬ ለመፍታት መሞከር ህይወትን ካለአግባብ ለመቆጣጠር መሞከር ነው፡፡ ጠቢብ ለነገ ዛሬ ያቅዳል ነገር ግን የነገን ለነገ ትቶ የዛሬን ዛሬ ይሰራዋል፡፡ ዛሬን ለመኖር ያለን ዛሬ ብቻ ነው፡፡
እንግዲህ እንደ ጥበበኞች እንጂ ጥበብ እንደሌላቸው ሳይሆን እንዴት እንድትመላለሱ በጥንቃቄ ተጠበቁ፤ . . . ዘመኑን ዋጁ። ኤፌሶን 5፡15-16
የፉክክር መድረኮች
ለእግዚአብሄር ክብር ተፈጥረናል፡፡ እግዚአብሄር ለልዩ አላማ ፈጥሮናል፡፡ አንዳችን ከሌላችን የተለየ ጥሪ አለን፡፡ እግዚአብሄር በህይወታችን ያስቀመጠውን ጥሪ መፈፀም የህይወት ምድብ ስራችንና ተልእኳችን ነው፡፡
እግዚአብሄር በህይወታችን ያስቀመጠው ሃይልና ፀጋ ለዚህ እግዚአብሄ ለጠራን ተልእኮ የሚበቃ ነው፡፡ ከዚህ ተልእኮ የሚተርፍና የሚባክን ምንም ተጨማሪ ሃይል የለንም፡፡
ከዚህ አንፃር እያንዳንዳችን እግዚአብሄር በውስጣችን ያስቀመጠውን ጥሪ መከተል እንጂ ከእኛ እጅግ የተለየ ጥሪ ካለው ከጎረቤታችን ጋር መፎካከር አይገባንም፡፡ ከጎረቤታችን ጋር መፎካከር ጥሪያችንን እንድንጥልና ፍሬ ቢስ እንድንሆን ያደርገናል፡፡
ከእኛ እጅግ የተለየ ጥሪ ካለው ከሌላው ሰው ጋር በመፎካከር እግዚአብሄር ከሰጠን ጥሪ ወደሃላ የሚጎትቱትን ነገሮች ፀንተን ልንቃወማቸው ይገባል፡፡
የአለምን አሰራር ተከትለን በኑሮ ትምህክት ወሰጥ እንድነጋባ የሚፈትኑትን ነገሮች ተቃቁመንና ከከንቱ ፉክክር ራሳችብን በፈቃዳችንም ራሳችንን አግልለን የተሰጠንን ሩጫ በትግስት እንሩጥ፡፡
እንግዲህ እነዚህን የሚያህሉ ምስክሮች እንደ ደመና በዙሪያችን ካሉልን፥ እኛ ደግሞ ሸክምን ሁሉ ቶሎም የሚከበንን ኃጢአት አስወግደን፥ የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን፥ በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ፤ እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአልና። ዕብራውያን 12፡1-2
ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን አትውደዱ፤ በዓለም ያለው ሁሉ እርሱም የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት ስለ ገንዘብም መመካት ከዓለም ስለ ሆነ እንጂ ከአባት ስላልሆነ፥ ማንም ዓለምን ቢወድ የአባት ፍቅር በእርሱ ውስጥ የለም።1ኛ ዮሐንስ 2፡15-16
በፈቃዳችን ራሳችንን ማግለል ያለብን የዘመናችን የፉክክር መድረኮች
1. በምንበላውና በምንጠጣው መመካት
ሰው ለእግዚአብሄር ክብር ከፍ ላለ ጥሪ ተፈጥሯል፡፡ ለእግዚአብሄር ክብር የማይኖር ሰው በመብላትና በመጠጣት ከመመካት ውጭ ሌላ የተሻለ ነገር ሊያደረግ አይችልም፡፡ ለእኛ የክርስቶስ ተከታዮች ግን እንደዚህ አይደለም፡፡ እኛ የምንበላው እና የምንጠጣው ለመብለጥ ሳይሆን የእግዚአብሄርን ፈቃድ በምድር ላይ ለማስፈፀም ነው፡፡ የእግዚአብሄርን ፈቃድ ለማገልገል በምንበላበትና በምንጠጣበት አራት ኮከብ ሆቴል አንፎካከርም፡፡
መብል ለሆድ ነው፥ ሆድም ለመብል ነው፤ እግዚአብሔር ግን ይህንም ያንም ያጠፋቸዋል። ሥጋ ግን ለጌታ ነው እንጂ ለዝሙት አይደለም፤ ጌታም ለሥጋ ነው፤ 1ኛ ቆሮንቶስ 6፡13
ለሚጠፋ መብል አትሥሩ፤ ነገር ግን ለዘላለም ሕይወት ለሚኖር መብል የሰው ልጅ ለሚሰጣችሁ ሥሩ፤ እርሱን እግዚአብሔር አብ አትሞታልና። ዮሃንሰ 6፡27
2. በምንለብሰው አንፎካከርም
ልብስ ሰውነትን ከመሸፈን ባለፈ በአለም ላይ ከፍተኛ የመፎካከሪያ መድረክ ነው፡፡ እከሌ የለበበሰወ ልብስ እንደዚህ አይነት ምልክት ነው፡፡ እከሌ ካለእንደዚህ አይነት ምርት ልብስ አይለብስም፡፡ እከሊት ቀሚስዋን የገዛችው በእንደዚህ አይነት ብር ነው በማለት ሰዎች ከሌሎች የበለጠ ለመልበስ ይፎካከራሉ፡፡ ይህ ለክርስቲያን እጅግ ያነሰና የማይገባ ፉክክር በመሆኑ ክርስትያን ከዚህ የልብስ የውድድር መድረክ በፍጥነት ራሱን ማግለል አለበት፡፡ እኛን ሊያለብሰብንና ከዚህ እግዚአብሄር ካለበሰን የሞገስ መጠን በላይ ሊያሳምረን የሚችል ብራንድ የለም፡፡
እግዚአብሔር ግን ዛሬ ያለውን ነገም ወደ እቶን የሚጣለውን የሜዳን ሣር እንዲህ የሚያለብሰው ከሆነ፥ እናንተ እምነት የጎደላችሁ፥ እናንተንማ ይልቁን እንዴት? ማቴዎስ 6፡30
3. በሚነዳው መኪና ውድነት መፎካከር
አለማዊያን ከቁሳቁስ ከፍ ያለ የሚወዳደሩበትር ነገር ስለሌላቸው በሚነዱት መኪና ይፎካከራሉ፡፡ በሚነዳው መኪና አይነትና ሞዴል ከማይመለከታቸው ሰዎች ጋር መፎካከር ለክርስቲያን የሚገባ አይደለም፡፡ የመኪና ጥቅም ሰውን ከ ሀ ወደ ለ ማድረስ ነው፡፡ እውነት ነው ልዩ እንክብካቤ የሚያስፈልጋው ሰዎች ተጨማሪ ምቾት ያለው መኪና ያስፈልጋቸዋል፡፡ የመኪናው ሞዴል ግን በመኪናው ተንቀሳቅሰን ከምንሰራ የእግዚአብሄር የአገልግሎት ጥሪ ይበልጥ መግነን የለበትም፡፡ ሰው ስለሚነዳው መኪና ከሌላው ጋር ከተፎካከረ በኑሮ ትህምክት ወጥመድ ውስጥ ወድቋል ማለት ነው፡፡
4. ስለሚይዘው ስልክ ውድነትና ጥራት
መሰረታዊው የስልክ ጥቅም ሰውን ከሰው ጋር በድምፅ ማገናኘት መሆኑ አንዳንዴ ይረሳል፡፡ ስለዚህ ሰው ውድ ያልሆነ ስልክ ስለያዘ ተደብቆ ስልኩን የሚያነሳው ከሆነ በማይገባው የህይወት ፉክክር ውስጥ ወድቋል ማለት ነው፡፡ ሰው ውድ ባልሆነ ስልክ ከተዋረደ በውድ ስልክ ይመካል ማለት ነው፡፡ አብዛኛው ሰው ከሚይዘው ስልክ 75 እጁን ቴክኖሎጂ እንደማይጠቀምበት የእያንዳንዳችን የዘወትር እይታ ምስክር ነው፡፡ ብዙ ሰው ከሰው እንዳላንስ ብሎ በሚገዛው ውድ ስልክ ውድ ያልሆነ ስልክ ከሚያደርግለት ነገር በላይ አይጠቀምበትም፡፡ እውነት የምትጠቀምበት ከሆነ ደግሞ ውድ ስልክ ያስፈልግሃል እግዚአብሄርም ይሰጥሃል፡፡
5. የመኖሪያ ቤት ውድነት ወይም አካባቢ
የሚኖርበት አካባቢ ለፉክክር የማይበቃ ስለሆነ አንገቱን አቀርቅሮ የሚገባና የሚወጣ ሰው ውድ ቦታ ቢኖር እንደማየመካ ምንም ማረጋገጫ የለውም፡፡ መኖሪያ ቤት ከመኖሪያ ቤትነት ባለፈ የሰው ልክ የሚለካበት ከሆነ አደጋ ነው፡፡ ልካችን የሚለካው በእግዚአብሄር ልጅነት ስለሆነ በዚህ በዘቀጠ የፉክክረ መድረክ ላይ በመገኘት በማይመጥነን ተራ ነገር ራሳችንን አናዋርድም፡፡
6. ስምና ዝና
ከእግዚአብሄር ልጅነት በላይ ስልጣን የለም ፡፡ ከንጉስ የቤተሰብ አባልነት በላይ ዝና የለም፡፡ እግዚአብሄር በላያችን ያስቀመጠው ዝናና ስልጣን ለጥሪያችን በቂ ነው፡፡ ጥሪያችንን ለመከተል በተሰጠን ጉልበት ዝናን በማግኘት ሩጫ ላይ አናባክነውም፡፡ ከዚህ በላይ ዝነኛ ለመሆን ከማንም ጋር መፎካከር ለእግዚአብሄር አገልጋይነታችን ክብር አይመጥንም፡፡
7. በልጆች ትምህርት ቤት
እኔ ልጆቼን የማስተምረው በወር ይህ ያህል እየከፈልኩ ነው፡፡ እኔ ደግሞ ይህን ያህል እከፍላለሁ፡፡ የእኔ ልጆች ትምህርት ቤት እንዲህ ነው እንዲያ ነው በማለት ሰዎች በልጆች ትምህርት ቤት ክፍያ ውድነት ይመካሉ፡፡
በእግዚአብሄር ከመመካት ውጭ ያለውን ትምክት እግዚአብሄር አይቀበለውም፡፡ በመክፈል ችሎታችን በተመካን ቁጥር ደግሞ እግዚአብሄር ልጆቻችንን እንዲባርክ ፣ ልባቸውን እንዲከፍትና እግዚአብሄር በወደፊታቸውና በተስፋቸው እንዲባርካቸው ጌታን ተስፋ ማድርግ ያቅተናል፡፡ ከጎረቤታችን ጋር በልጅ ትምህርት ቤት ፉክክረ ውስጥ ሳንገባ ፣ ሳንጨነቅ መክፈል የምንችለውን በአቅማችን እየከፈልን ስለ ልጆቻችን ወደፊት በእግዚአብሄርት መታመን ይገባናል፡፡
እኔም ተመለስሁ፥ ከፀሐይ በታችም ሩጫ ለፈጣኖች፥ ሰልፍም ለኃያላን፥ እንጀራም ለጠቢባን፥ ባለጠግነትም ለአስተዋዮች፥ ሞገስም ለአዋቂዎች እንዳልሆነ አየሁ፤ ጊዜና እድል ግን ሁሉን ይገናኛቸዋል። መክብብ 9፡11
ስምንተኛውን በመጨመር ለፅሁፉ አስተዋፅኦ ያድርጉ፡፡
በህይወታችን እግዚአብሄር ያስቀመጠውን አላማ ለመፈፀም መብዛት አይጠይቅም፡፡ በምድር ላይ የተፈጠርንበትን የህይወት አላማ ላለመፈፀም ደግሞ መዋረድ አያግደንም፡፡ የእግዚአብሄርን ሃሳብ አገልገለን ለማለፍ የሚያስፈልገን የእግዚአብሄር ሃይል ብቻ ነው፡፡
መዋረድንም አውቃለሁ መብዛትንም አውቃለሁ፤ በእያንዳንዱ ነገር በነገርም ሁሉ መጥገብንና መራብንም መብዛትንና መጉደልን ተምሬአለሁ። ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ። ፊልጵስዩስ 4፡12-13
የተጠራነው ለአንድ ነገር ብቻ አይደለም
ሁላችንም ለእግዚአብሄር ክብር ተፈጥረናል፡፡ እግዚአብሄር በእያንዳንዳችን ህይወት ሊሰራ ያለው ልዩ አላማ አለ፡፡ ለዚያ አላማ ተጠርተናል፡፡ እግዚአብሄር ለምን አላማ እና አገልግሎት እንደጠራን ማወቅን የመሰለ በህይወት የሚያሳርፍና የሚያረጋጋ ነገር የለም፡፡ ጥሪያችንን ስናውቅ በጥሪያችን ላይ ብቻ እናተኩራለን፡፡ ጥሪያችንን ስናውቅ የተከፈቱ እጅግ ብዙ በሮች ውስጥ አንገባም፡፡ ጥሪያችንን ስናውቅ ከሙከራ እንድናለን፡፡ ጥሪያችንን ስናውቅ ህይወትን መኖር እንጀምራለን፡፡
ጥሪያችን የሆነውን ነገር ማወቅ በጣም አስፈላጊ እንደሆነ መጠን ጥሪያችን ያልሆነውን ነገር ማወቅም በጣም አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ ጥሪያችንን ስናውቅ ጥሪያችን ያልሆነውን እንለያለን፡፡ ማን እንደሆንን ስንረዳ መን እንዳልሆንን ይገባናል፡፡ እሺ የምንለውን ስናውቅ እምቢ የምንለውን እናውቃለን፡፡ ጥሪያችንን ስናውቅ ውስን የሆነውን ጊዜያችንን ጉልበታችንን እውቀታችንን ገንዘባችንን ባልተጠራንበት ነገር ላይ ከማፍሰስ እንድናለን፡፡ ጥሪያችንን ስናውቅ ምንም ብንጥር ፍሬ ከማናፈራበት ቦታ እንርቃለን፡፡
እውነተኛ ፍሬ የሚፈራው በእድል አይደለም፡፡ ፍሬ የሚፈራው በቅልጥፍና አይደለም፡፡ ፍሬ የሚፈራው ጥሪን አውቆ በመከተል ነው፡፡
ጥሪያችንን ስናውቅ ማድረግ የማንችለውን እንድናውቅ ለዚያ ለተጠሩት እንድንተወው ያስችለናል፡፡ ጥሪያችን ስናውቅ ራሳችንን ትሁት አድርገን ለተጠሩት ሰዎች እንድንተው ይረዳናል፡፡ ጥሪያችንን ስናውቅ ከእኛ የተሻለ ለሚሰሩት በመተው በራሳችን ጥሪ ላይ እንድናተኩር ያስችለናል፡፡
ጥሪያችንን ስናውቅ ጥሪያችን ያልሆነው ውስጥ ገብተን ጥሪያቸው ከሆኑ ሰዎች ጋር እንዳንጣላ ይጠብቀናል፡፡ ጥሪያችንን ስናውቅ ጥሪያችን ያልሆነው ውስጥ ገብተን ጥሪያቸው የሆኑትን ሰዎች እንዳናስተጓጉል ይጠብቀናል፡፡ ጥሪያችንን ስናውቅ በራሳችን ጥሪ ላይ አተኩረን ጥሪያችንን በትጋት እንድንፈፅም ያደርገናል፡፡ ጥሪያችንን ስናውቅ ለጥሪያችን ብቻ ተለክቶ የተሰጠንን የእግዚአብሄር ፀጋ በአግባቡ እንድንጠቀምበት ያደርገናል፡፡
ጥሪያችንን በሚገባ ካልተረዳንና ያየነውና የሰማነው ጥሪ ሁሉ የሚያመረን ከሆነ መኪናን እንደመንዳት ሳይሆን እንደመግፋት ይሆንብናል፡፡ በህይወታቸን የሚለቀቀው የእግዚአብሄር ፀጋ የጥሪያችን አይነትና ልክ ስለሆነ የእግዚአብሄርን ስራ በጭንቀት ሳይሆን በደስታ እናደርገዋለን፡፡ በህይወታችን ያለው የእግዚአብሄር ፀጋ ስለማያንስና ስለማይበዛ ለጥሪያችን ብቻ የሚበቃ ስለሆነ የሚረዳንና የሚያከናውንልን በጥሪያችን ላይ ብቻ ስንቆም ነው፡፡ ባለተጠራንበት ቦታ ቆመን የእግዚአብሄር ፀጋ ይደግፈናል ማለት የማይታሰብ ነገር ነው፡፡
ሰው እግዚአብሄር እንደሚያስችለው እና እንደሚያበረታው እንደሚያውቀው ሁሉ ለሁሉም ነገር ደግሞ እንዳልተጠራ ማወቁ ወሳኝ ነው፡፡ የእርሱ ጥሪ በጣም ልዩ ከመሆኑ የተነሳ ሁሉንም ነገር ማድረግ የሚችል የሚመስለው ሰው ተታሏል፡፡ በእግዚአብሄር ነገር እየበሰለን ስንሄድ የምንረዳው በጣም አስፈላጊ ነገር ማድረግ የምንችለው በጣም ውስን ነገር ብቻ እንደሆነ መረዳት ነው፡፡ በዚያ በተጠራንበት ውስን ነገር ላይ ከተወሰንን ፍሬያማ እንሆናለን፡፡
በጥሪያችን ስትቆም እርሱ መሰረታዊ ፍላጎታችን ነው ፣ ሞገሳችን ነው ፣ ውበታችን ነው ፣ ዝናችን ነው ፣ እውቅናችን ነው ፣ እርካታችን ነው እንዲሁም ደስታችን ነው፡፡ የተሳካልህ ለመሆን የራስህ ጥሪ ማድርግ በቂ ነው፡፡ እንዲከናወንልህ የሌላን ሰው ጥሪ ማድረግ እና እንደምትችለው ማሳየት የለብህም፡፡
ብቻ ለእያንዳንዱ እግዚአብሔር እንደ ከፈለለት እያንዳንዱም እግዚአብሔር እንደ ጠራው እንዲሁ ይመላለስ። እንዲሁም በአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ እደነግጋለሁ። 1ኛ ቆሮንቶስ 7፡17