እግዚአብሄር ከዘላለም ንጉስ ነው፡፡ እግዚአብሄር ከዘላለም እስከዘላለም ነው፡፡ እግዚአብሄር መጀመሪያና መጨረሻ የለውም እግዚአብሄር አልፋና ኦሜጋ ነው፡፡
አልፋና ዖሜጋ፥ ፊተኛውና ኋለኛው፥ መጀመሪያውና መጨረሻው እኔ ነኝ። ራእይ 22፡13
የእግዚአብሄር ከዘላለም እስከ ዘላለም መሆኑ በአእምሮዋችን እየመረመርም፡፡ የእግዚአብሄር ዘላለማዊነት በአእምሮዋችን ከመረዳት ያለፈ ነው፡፡ የእግዚአብሄር ዘለዓለማዊነት ስፋቱና ርዝመቱ ከፍታውም ጥልቅነቱም ምን ያህል መሆኑን ለማስተዋል ያልፋል፡፡
እነሆ፥ እግዚአብሔር ታላቅ ነው፥ እኛም አናውቀውም። የዘመኑም ቍጥር አይመረመርም። ኢዮብ 36፡26
እግዚአብሄር የዘላለም አምላክነቱና እንደማይመረመርና ሰዎችም ሁሌ በእርሱ እንዲታመኑ የሚያዘው፡፡
አላወቅህምን? አልሰማህምን? እግዚአብሔር የዘላለም አምላክ፥ የምድርም ዳርቻ ፈጣሪ ነው፤ አይደክምም፥ አይታክትም፥ ማስተዋሉም አይመረመርም። ኢሳያስ 40፡28
እግዚአብሄር የዘላለም አምላክና ማስተዋሉም የማይመረመር ስለሆነ በእግዚአብሄር ላይ ከመደገፍ የተሻለ ነገር የለም፡፡ እግዚአብሄር የዘላለም አምላከ ነው፡፡ የዘላለም ክንዶች ከእኛ በታች ናቸው፡፡ ከዚህ በላይ የሚያኮራና ሳንናወጥ ረጋ ብለን እንንድንኖር የሚያደርግን እውቀት የለም፡፡
መኖሪያህ የዘላለም አምላክ ነው፥ የዘላለምም ክንዶች ከአንተ በታች ናቸው፤ ጠላትህን ከፊትህ አውጥቶ፦ አጥፋው ይላል። ዘዳግም 33፡27
እግዚአብሄር በድንገት በህዝብ ድምፅ ብልጫ የተመረጠ ፕሬዝዳንት አይደለም፡፡ እግዚአብሄር ከዘላለም ንጉስ ነው፡፡
መንግሥትህ የዘላለም መንግሥት ናት፥ ግዛትህም ለልጅ ልጅ ነው። መዝሙር 145፡13
እግዚአብሔር ግን እውነተኛ አምላክ ነው፤ እርሱም ሕያው አምላክና የዘላለም ንጉሥ ነው፤ ከቍጣው የተነሣ ምድር ትንቀጠቀጣለች፥ አሕዛብም መዓቱን አይችሉም። ኤርምያስ 10፡10
ከእግዚአብሄር ከዘላለም ከመኖር አንፃር የሰው በምድር ላይ ቆይታው እጅግ በጣም አጭር ነው፡፡ የሰውን በስጋ ቆይታ መፅሃፍ ቅዱስ ከእንፍዋለት ጋር ያነፃፅረዋል፡፡ የምድር ህይወት እጅግ አጭር በመሆኑ በራስ ላይ ከመደገፍ በላይ አክሳሪ ነገር የለም፡፡ በዘላለም አምላክ በእግዚአብሄር ላይ ከመደገፍ በላይ ጥበብ የለም፡፡
ሕይወታችሁ ምንድር ነው? ጥቂት ጊዜ ታይቶ ኋላ እንደሚጠፋ እንፍዋለት ናችሁና። ያዕቆብ 4፡14
ከእግዚአብሄር ዘላለማዊነት አንፃር የምድር ቆይታችን ነጥብ አትሞላም፡፡ የዘላለም አምላከ እግዚአብሄር አምባችን ነው፡፡
ጌታ እግዚአብሔር የዘላለም አምባ ነውና ለዘላለም በእግዚአብሔር ታመኑ። ኢሳያስ 26፡4
ሰው ማንንም ባያምን እግዚአብሄርን ማመን ግን ግዴታ ነው፡፡ በዘላለም አምላክ በእግዚአብሄር ላይ ካልተደገፍን በማንም ላይ መገደፍ አንችልም፡፡
Month: April 2021
መኖርን እስቲ አንርሳ
ከዚያ ደግሞ ኮሌጅን ለመጨረስ እና ሥራ ለመጀመር እስከሞት ድረስ እጓጓ ነበር፡፡
ከዚያም ለማግባት እና ልጆች ለመውለድ እስከሞት ድረስ እጓጓ ነበር፡፡
ከዚያ በኋላ ወደ ሥራዬ መመለስ እንድችል ልጆቼን ለትምህርት የሚያበቃ ዕድሜዬ እንኪደርሱ እስከሞት ድረስ እጓጓ ነበር፡፡
ከዚያ በኋላ ጡረታ ለመውጣት እስከሞት ድረስ እጓጓ ነበር፡፡
እና አሁን ለመሞት ተቃርቤያለሁ . . .
በድንገት የተረዳሁት ነገር በህይወቴ ዘመን ሁሉ የሚቀጥለው ደረጃ ላይ ለመድረስ እጅግ ስጓጓ ነገር ግን መኖርን ረስቼ እንደነበር ነው፡፡ ይላል አንድ የእድሜ ባለጠጋ ሰው፡፡
ይህ የሁላችንም ፈተና ነው፡፡ ሁላችንም አንድ ደረጃ ላይ መድረስ ፣ አንድን ግኝት ማግኘት ፣ ስኬት ላይ መድረስና በያዝነው ነገር ድልን መቀዳጀት እንፈልጋለን፡፡
ይህ በጣም አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ በህይወት መትጋት መፅሃፍ ቅዱሳዊ መርሆ ነው፡፡
ነገር ግን መትጋት ብቻ ሳይሆን የተጋንበትን ነገር ማጣጣም እንዲሁ መፅሃፍ ቅዱሳዊ መርህ ነው፡፡ ማግኘት ብቻ ሳይሆን ያገኘነውን ነገር ጊዜ ወስደን ማጣጣም መጠቀምና በዚያ መደሰት መፅሃፍ ቅዱሳዊ ትእዛዝ ነው፡፡
ማግኘት አንድ ነገር ነው ያገኘነውን መጠቀም ሌላ ነገር ነው፡፡ እንድናገኝ ብቻ ሳይሆን ያገኘነውን ነገር እንድንጠቀንም እግዚአብሄር ይፈልጋል፡፡
አንዳንድ ሰው ገንዘብን ለማግኘት እጅግ ሲጥር ታዩታላችሁ፡፡ ጥረቱም ይሳካለታል ገንዘብን ያገኛል፡፡ በመሃል ግን ገንዘብን ለማግኘት የሰራበትንና የለፋበትን ምክኒያት ይረሳዋል፡፡ ገንዘቡን አይጠቀምበትም፡፡ ገንዘቡ ህይወቱን አያመቻችለትም፡፡ ገንዘቡ መሰረታዊ ፍላጎቱ አያሟላለትም፡፡ ገንዘቡን ያከማቸዋል፡፡ ገንዘቡን በማየት ብቻ ይረካል፡፡ ገንዘቡ የተጠራቀመበት ምክኒያት ይጠፋል፡፡ ገንዘቡ ጥቅም ላይ አይውልም፡፡ ገንዘቡ ባለገንዘቡን ሳይረዳው ይቀራል፡፡
የዚህ ሰው ችግሩ ገንዘብ መስራት ያውቃል ነገር ግን ገንዘቡን መጠቀም አልተማረም፡፡ ገንዘብ ለመስራት ሰልጥኗል ገንዘብን ለመጠቀም አልሰለጠነም፡፡ ገንዘቡን እንዴት እንደሚያገኘው እውቀት አለው ገንዘቡን እንዴት በሚገባ እንደሚጠቀምበት እውቀት ይጎድለዋልን፡፡
እግዚአብሄርን የማያውቁ ሰዎች በዚህ እጅግ ይቸገራሉ፡፡ ያገኙትን ገንዘብ ወይ ሳይጠቀሙበት አካብተውት አካብተውት ያልፋሉ፡፡ ደስታቸውን ሁልጊዜ ለወደፊት ያስተላለፉታል፡፡ ይህ ሲሆንልኝ መደሰት እጀመራለሁ ይላሉ፡፡ ልክ እንደደረሱበት ሲያውቁ አሁን ያሉበት ደረጃ በራሱ ግኝትና ስኬት እንደሆነ ይዘነጉታል፡፡ ዛሬ ያሉበትን ደረጃ ይንቁታል፡፡ በዛሬ ባሉበት ደረጃ መደሰት አያውቁም፡፡ ዛሬ ላይ ሲደርሱ ስለማያውቁት ስለነገ ይጓጓሉ፡፡ ዛሬ ላይ ሲደርሱ የዛሬን ድል እርግፍ አድርገው ትተው ሳይደሰቱበት ስለነገ ብቻ ማውራት መጨነቅ ማሰብ ይጀምራሉ፡፡ ስለዚህ ነው ህይወታችንን በቀን ከፋፋልን እንድንደሰትበት መፅሃፍ ቅዱስ የሚያስተንምረን፡፡
ነገ ለራሱ ይጨነቃልና ለነገ አትጨነቁ፤ ለቀኑ ክፋቱ ይበቃዋል። የማቴዎስ ወንጌል 6፡34
ህይወት በትጋት የምንወጣው ሃላፊነት ብቻ ሳይሆን ቀስ ብለን የምንደሰትበት ስጦታ ነው፡፡
የእግዚአብሄ ስጦታ ሁለት ነው፡፡ እግዚአብሀር በህይወት አንዲከናወንልን ትጋትን ይሰጠናል፡፡ ይህም ብቻ ሳይሀነ የደረስብነትን ግኝት ረጋ ብለን እንድናጣጠምው እውቀትን ይሰጠናል፡፡
ከሚበላውና ከሚጠጣው ደስም ከሚለው በቀር ለሰው ከፀሐይ በታች ሌላ መልካም ነገር የለውምና እኔ ደስታን አመሰገንሁ፤ ከፀሐይም በታች ከድካሙ እግዚአብሔር በሰጠው በሕይወቱ ዘመን ይህ ደስታው ከእርሱ ጋር ይኖራል።መጽሐፈ መክብብ 8፡15
እግዚአብሔር ሥራህን ተቀብሎታልና ሂድ፥ እንጀራህን በደስታ ብላ፥ የወይን ጠጅህንም በተድላ ጠጣ። ሁልጊዜ ልብስህ ነጭ ይሁን፤ ቅባትም ከራስህ ላይ አይታጣ። በሕይወትህ፥ አንተም ከፀሐይ በታች በምትደክምበት ድካም ይህ እድል ፈንታህ ነውና ከንቱ በሆነ በሕይወትህ ዘመን ሁሉ፥ ከፀሐይ በታች በሰጠህ፥ በከንቱ ዘመንህ ሁሉ፥ ከምትወድዳት ሚስትህ ጋር ደስ ይበልህ። መጽሐፈ መክብብ 9፡7-9
የህይወት ለውጥ መፈለግ ብቻ አይበቃም
የእስራኤል ህዝብ በውሃ እጦት በተሰቃየበት ጊዜ እግዚአብሄር ውሃን እንደሚያመጣ በነቢዩ ተናገራቸው፡፡ ነገር ግን ውሃ ከመምጣቱ በፊት ውሃውን የሚይዘውን ጉድጓድ እንዲቆፍሩም ተናገራቸው፡፡
እንዲህም አለ፦ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በዚህ ሸለቆ ሁሉ ጕድጓድ ቆፈሩ። እግዚአብሔርም እንዲህ ይላል፦ ነፋስ አታዩም፥ ዝናብም አታዩም፥ ይህ ሸለቆ ግን ውኃ ይሞላል፤ እናንተም ከብቶቻችሁም እንስሶቻችሁም ትጠጣላችሁ። 2ኛ ነገሥት 3፡16-17
ይህ ታሪክ በህይወታችን ለሚመጣው ታእምር የሚመጥን ነገር መዘጋጀት እንዳለበት ያስተምረናል፡፡ አሁን ያለን ነገር ካልተለወጠ ወደፊታችን ሊለወጥ አይችልም፡፡ ህይወታችን የሚመጣውን በረከት ለመያዝ እንዲችል አድርጎ ካልተለወጠ በረከተን መጠበቅ መጠበቅ ሞኝነት ነው፡፡ አሁን ያለን የህይወት ደረጃ ወደፊት የሚመጣውን ሃላፊነትና ስልጣን ሊሸከም አይችልም፡፡ አሁን ያለን የመያዝ አቅም ነገ ሊመጣ ያለውን በረከት ሊይዝ አይችልም፡፡ አሁን ለነገ ህይወታችን ካልተለወጠ ነገ የሚመጣወን ከፍታ መያዝ ያቅተዋል፡፡
በአረጀ ልብስ አዲስ እራፊ የሚጥፍ የለም፤ ቢደረግ ግን፥ አዲሱ መጣፊያ አሮጌውን ይቦጭቀዋል፥ መቀደዱም የባሰ ይሆናል። በአረጀ አቁማዳም አዲስ የወይን ጠጅ የሚያኖር የለም፤ ቢደረግ ግን፥ የወይን ጠጁ አቁማዳውን ያፈነዳል የወይኑም ጠጅ ይፈሳል አቁማዳውም ይጠፋል አዲሱን የወይን ጠጅ ግን በአዲስ አቁማዳ ያኖራሉ። ማርቆስ 2፡21-22
አሁን ያለንበት የህይወት ደረጃ እግዚአብሄር ይመስገን አሁን ላለንበት ሃላፊነት በቂ ነው፡፡ አሁን የደረስንበት የህይወት ደረጃ አሁን ላለን ስልጣን በቂ ነው፡፡ አሁን ያለንበት የህይወት ደረጃ አሁን ላለን ተፅእኖ መጠን በቂ ነው፡፡
ነገር ግን እኛ ማደግ እንፈልጋለን፡፡ እኛ ማደግ ከምንፈልገው በላይ እግዚአብሄር እንድናድግ ይፈልጋል፡፡ እግዚአብሄር እኛን መለወጥ ይፈልጋል፡፡ እግዚአብሄር አዲስን ነገር ማድረግ ይፈልጋል፡፡
እነሆ፥ አዲስ ነገርን አደርጋለሁ፤ እርሱም አሁን ይበቅላል፥ እናንተም አታውቁትምን? በምድረ በዳም መንገድን በበረሀም ወንዞችን አደርጋለሁ። ኢሳይያስ 43፡19
አሁን ባለን የህይወት ደረጃ መኖር የምንችለው አሁን ላለው ህይወት ብቻ ነው፡፡ አሁን ባለን የህይወት አቅም መያዝ የምንችለው አሁን ያለንን ስልጣን ብቻ ነው፡፡ አሁን ባለን የህይወት ብስለት ማስተናገድ የምንችለው የአሁኑን የህይወት ደረጃ ብቻ ነው፡፡ ለማደግና መለወጥ ወሳኝ ነው፡፡ ስለነገ ዛሬ መስራት ወሳኝ ነው፡፡
የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም በጎና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም የሆነው ነገር ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ። ሮሜ 12፡2
ለመድረስ ለምንፈልገው የህይወት ልክ ሌላ የህይወት ደረጃ ልክ ይጠይቃል፡፡ ለመድረስ ለምንፈልገው የስልጣን ልክ ሌላ የብስለት ደረጃ ይጠይቃል፡፡ ለመድረስ ለምንፈልገው የህይወት ከፍታ ሌላ የባህሪ ደረጃ ይጠይቃል፡፡
መድረስ ወደምንፈልግበት የህይወት ደረጃ ከፍ ለማለት መለወጥ ግድ ይላል፡፡ ወደምናየው የህይወት ከፍታ ለመውጣት መለወጥ ወሳኝ ነው፡፡ ወዳየንበት የህይወት የስልጣን ደረጃ ለመድረስ ይህ ያለንበት ህይወት ሊለወጥ ይገባዋል፡፡
ባለንበት ህይወት ከፍ ያለ ደረጃ መጠበቅ ሞኝነት ነው፡፡ ባለንበት ብስለት ከፍ ያለ ስልጣን መለማመድ የማይቻል ነው፡
በእግዚአብሔር ስም መጠራት
ከየትኛውም ከሚታዩ በረከቶች በላይ የሚያስደስተን ፣ የሚያረካንና ልባችንን የሚያሳርፈው የእግዚአብሄር ከእኛ ጋር የመኖሩ አውቀት ነው፡፡ ሲጀመር ለእግዚአብሄር ክብር ነው የተፈጠርነው፡፡ እኛ የራሳችን አይደለንም፡፡ እኛ የእግዚአብሄር ነን፡፡ የህይወታችን ባለቤት እግዚአብሄር ነው፡፡
እግዚአብሄር አብሮን እንዳለ ካወቅን አንፈራም፡፡ በሚያስፈራ ነገር ውስጥ ለማለፍ የምንደፍረው አግዚአብሄር ከእኛ ጋር እንዳለ ስናውቅ ብቻ ነው፡፡ የእግዚአብሄርን አብሮነት ከተረዳን በሞት መካከል እንኳን ካለፍርሃት እናልፋለን፡፡
በሞት ጥላ መካከል እንኳ ብሄድ አንተ ከእኔ ጋር ነህና ክፉን አልፈራም፤ በትርህና ምርኵዝህ እነርሱ ያጸናኑኛል። መዝሙር 23፡4
በማይመስል ሁኔታ ውስጥ በፀጥታ የምናልፈው ከምትችሉት በላይ እንድትፈትኑ የማይፈቅ እግዚአብሄር ተብሎ የተጻፈለት ጌታ ከእኛ ጋር እንዳለ በእርሱ እውቅና በከፍታና በዝቅታ እንደምናልፍ ስናውቅ ነው፡፡
ለሰው ሁሉ ከሚሆነው በቀር ምንም ፈተና አልደረሰባችሁም፤ ነገር ግን ከሚቻላችሁ መጠን ይልቅ ትፈተኑ ዘንድ የማይፈቅድ እግዚአብሔር የታመነ ነው፥ ትታገሡም ዘንድ እንድትችሉ ከፈተናው ጋር መውጫውን ደግሞ ያደርግላችኋል። 1ኛ ቆሮንቶስ 10፡13
የምናደርገው ነገር ሃሳቡ የእርሱ እንደሆነ ከተረዳንና እግዚአብሄር አብሮን እንዳለ ስለምናውቅ ምንም መንገዱ አስቸጋሪ ቢሆን እኛም መውጣት መዋጋት መውረስ እንፈልጋለን፡፡ እግዚአብሄር የምናደርገውን ነገር እንደመራን ካላወቅን ግን እኛም አብረን መውጣት አንፈልግም፡፡
እርሱም፦ አንተ ከእኛ ጋር ካልወጣህስ፥ ከዚህ አታውጣን። ዘፀአት 33፡15
ስለዚህ ነው እግዚአብሄር ከእኛ ጋር ከሆነ ማንም እንደማይቋቋመን መፅሃፍ ቅዱስ የሚያስተምረን፡፡
እግዚአብሄር ከእኛ ጋር ከሆነ ማን ይቃወመናል ሮሜ 8:31
እግዚአብሄርን የማይሰማ ነገር እንደሌለ እግዚአብሄር ሲልከን እና ከእኛ ጋር ሲሆን ሁሉም ነገር እግዚአብሄር በእኛ ወስጥ ለአስቀመጠው አላማ መሳካት ይገዛል፡፡
አሁንም ያዕቆብ ሆይ፥ የፈጠረህ፥ እስራኤልም ሆይ፥ የሠራህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ተቤዥቼሃለሁና አትፍራ፤ በስምህም ጠርቼሃለሁ፥ አንተ የእኔ ነህ። በውኃ ውስጥ ባለፍህ ጊዜ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፥ በወንዞችም ውስጥ ባለፍህ ጊዜ አያሰጥሙህም፤ በእሳትም ውስጥ በሄድህ ጊዜ አትቃጠልም፥ ነበልባሉም አይፈጅህም። ኢሳይያስ 43፡1-2