በምድር ላይ ህዝብን የሚያስተዳድርና የሚገዛ መንግስት እንዳለ ሁሉ በመካከላችን የእግዚአብሔር መንግስት አለ ይህም የእግዚአብሔር መንግስት የሚገለጥባት ቤተክርስቲያን ነች፡፡ የእግዚአብሔር መንግስት በአይን የማይታይ በስፍራ የማይወሰን መንግስት ነው፡፡ የእግዚአብሔር መንግስት መሪ ያለው ህዝብና የራሱ የአሰራር ህግ ያለው መንግስት ነው፡፡
ፈሪሳውያንም፦ የእግዚአብሔር መንግሥት መቼ ትመጣለች ብለው ቢጠይቁት፥ መልሶ፦ የእግዚአብሔር መንግሥት በመጠባበቅ አትመጣም፤ ደግሞም፦ እንኋት በዚህ ወይም፦ እንኋት በዚያ አይሉአትም። እነሆ፥ የእግዚአብሔር መንግሥት በመካከላችሁ ናትና አላቸው። ሉቃስ 17፡20-21
በተቃራኒው አለም ማለት ሰይጣን የሚገዛበት የአሰራር ስርአት ነው፡፡ አለም ማለት ከተማ ማለት ሳይሆን ሰው ባራሱ ላይ ጌታ የሆነበትና የሰው አስተሳሰብ የሚስተናገድበት ከእግዚአብሔር መንግስት ተቃራኒ የኑሮ ዘይቤ ነው፡፡
ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን አትውደዱ፤ በዓለም ያለው ሁሉ እርሱም የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት ስለ ገንዘብም መመካት ከዓለም ስለ ሆነ እንጂ ከአባት ስላልሆነ፥ ማንም ዓለምን ቢወድ የአባት ፍቅር በእርሱ ውስጥ የለም። 1ኛ ዮሐንስ 2፡15-16
የእግዚአብሔር መንግስት አስተሳሰብና የአለም(የሰው) አስተሳሰብ እጅግ የተለያዩ ናቸው፡፡
ዓለሙም ምኞቱም ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል። 1ኛ ዮሐንስ 2፡17
የአለም ወይም የሰው ስንል ከእግዚአብሔር ቃል የተቃረነ የአስተሳሰብ ዘይቤና ዋጋ አመለካከት ነው፡፡
የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም በጎና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም የሆነው ነገር ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ። ሮሜ 12፡2
የእግዚአብሔር መንግስት አስተሳሰብ ከአለም(ከሰው) አስተሳሰብ የሚለይበት ብዙ መንገዶች መንገዶች አሉ ከእነዚህም ውስጥ፡፡
• የፍቅርና ራስ ወዳድነት አስተሳሰብ
የእግዚአብሔር መንግስት አስተሳብ የእግዚአብሔር የሆነውንና ሰውን ሁሉ የመውደድ አስተሳሰብ ነው፡፡ ከእግዚአብሔርና ከሰው ጋር በአክብሮት የምንኖርበት ስርአት ነው፡፡ የአለም (የሰው) መንግስት ግን ራስ ተኮር የሆነ እያንዳንዱን ነገር ከግል ጥቅም አንፃር ብቻ የሚመዘንበት ስርአት ነው፡፡
እርሱ ከጨለማ ሥልጣን አዳነን፥ ቤዛነቱንም እርሱንም የኃጢአትን ስርየት ወዳገኘንበት ወደ ፍቅሩ ልጅ መንግሥት አፈለሰን። ቆላስይስ 1፡13-14
• የብርሃንና የጨለማ መንግስት
የእግዚአብሔር መንግስት በእግዚአብሔር ምሪት የተሞላ ነው፡፡ የአለም መንግስት ግን የእግዚአብሔር ምሪት የሌለበት ሰዎች መቼ እንደሚደናቀፉ የማያውቁበት የጨለማ መንግስት ነው፡፡ የእግዚአብሔር መንግስት የግልፅነት መንግስት ሲሆን የአለም መንግስት ድብቅ መንግስት ነው፡፡
ብርሃንም ወደ ዓለም ስለ መጣ ሰዎችም ሥራቸው ክፉ ነበርና ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ስለ ወደዱ ፍርዱ ይህ ነው። ክፉ የሚያደርግ ሁሉ ብርሃንን ይጠላልና፥ ሥራውም እንዳይገለጥ ወደ ብርሃን አይመጣም፤ እውነትን የሚያደርግ ግን ሥራው በእግዚአብሔር ተደርጎ እንደ ሆነ ይገለጥ ዘንድ ወደ ብርሃን ይመጣል። ዮሃንስ 3፡19-21
• የእውነትና የሃሰት አስተሳሰብ
የእግዚአብሔር መንግስት የእውነት መንግስት ነው፡፡ የእግዚአብሔር መንግስት ከእግዚአብሔርን ቃል የመጀመሪያውን የእግዚአብሔርን ሃሳብ የሚከተል መንግስት ነው፡፡ የአለም አሰራር ግን ላይ ላዩን ብቻ ማስተካከል የሚፈልግ ውስጡን ግን የማያጠራ የሃሰት ማስመሰያ አስተሳሰብ ነው፡፡ የአለም አስተሳሰብ ውጭውን ብቻ በማሳመር የሚያታልል ሲሆን የእግዚአብሔር መንግስት ትኩረቱ የውስጥ የልብ ንፅህና ነው፡፡
ብዘገይ ግን፥ በእግዚአብሔር ማደሪያ ቤት መኖር እንዴት እንደሚገባ ታውቅ ዘንድ እጽፍልሃለሁ፤ ቤቱም የእውነት ዓምድና መሠረት፥ የሕያው እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ነው። 1ኛ ጢሞቴዎስ 3፡15
• ማገልገልና የመገልገል መንገድ
በእግዚአብሔር መንግስት ባለን ነገር ሁሉ ለማገልገልና ሌሎችን ለመጥቀም የምንኖረው ኑሮ ሲሆን የአለም አስተሳሰብ በስልጣናችን ተጠቅመን ለመጠቀምና ሰዎች እንዲያገለግሉንና እንዲጠቅሙን የምንሄድበት አስተሳሰብ ነው፡፡
• የመዝራትና የማከማቸት አስተሳሰብ
የእግዚአብሔር መንግስት የመዝራትና የመስጠት አስተሳሰብ ነው፡፡ የእግዚአብሔር መንግስት ሌሎችን በመባረክና በማንሳት ቤተክርስቲያንን በማገልገል የሚረካ አስተሳሰብ ነው፡፡ በአለም ግን ሰው ደህንነት የሚሰማው ሲያከማች ሲሰበስብ ነው፡፡
ብልና ዝገት በሚያጠፉት ሌቦችም ቆፍረው በሚሠርቁት ዘንድ ለእናንተ በምድር ላይ መዝገብ አትሰብስቡ፤ ነገር ግን ብልም ዝገትም በማያጠፉት ሌቦችም ቆፍረው በማይሠርቁት ዘንድ ለእናንተ በሰማይ መዝገብ ሰብስቡ፤ ማቴዎስ 6፡19-20
• የይቅርታና የበቀል አካሄድ
የእግዚአብሔር መንግስት የምህረትና የይቅርታ መንግስት ነው፡፡ የእግዚአብሔር መንግስት በእጅጉ ይቅር የተባሉ ሰዎች በተራቸው ሌላውን ይቅር ለማለት የተዘጋጁ ሰዎች መንግስት ነው፡፡ የአለም መንግስት ግን የበቀልና የተንኮል አስተሳሰብ የገነነበት ሲሆን አንዱ በሌላው ላይ ተረማምዶ ወደላይ ከፍ የሚልበት ክፉ አሰራር ነው፡፡ በአለም አስተሰታሳብ በፊትህ የሚቆመውን አስወግደህ ማለፍ አዋቂነት ነው፡፡
• የመተባበርና የፉክክር አስተሳሰብ
በእግዚአብሔር መንግስት ለሌላው መነሳትና ማሸነፍ በደስታ የሚሰራበት ሲሆን በአለም አሰራር ግን ሌላውን በመጣል ከሌላው በላይ ከፍ ብሎ ለመታየት በትእቢት የሚኬድበት የአሰራር ዘይቤ ነው፡፡ የእግዚአብሔር መንግስት የሌላውን ጉድለት ለመሙላት የመሄድ አስተሳሰብ ሲሆን የአለም አስተሳሰብ ሌላው ሁሉ ለእርሱ እንዲሰራለት ራስን ብቸኛ እንደተመረቀ መቁጠር ነው፡፡
• ዘላለማዊና ጊዜያዊ አስተሳሰብ
የእግዚአብሔር መንግስት አስተሳሰብ የሚመዘነው በዘላለማዊ እይታው ነው፡፡ የእግዚአብሔር መንግስት ዜጋ ለዘላለም ከእግዚአብሔር ጋር እንደሚኖር የእግዚአብሔር ልጅ ጊዜያዊውን ደስታ ንቆ የሚኖረበት ህይወት ነው፡፡ የአለም አስተሳሰብ ግን ለጊዜያዊው ነገር ህይወትን የማባከን ህይወት ነው፡፡
• የትህትናና የትእቢት አስተሳሰብ
የእግዚአብሔር መንግስት መዋረድና የዝቅታን አስተሳሰብን ሲያስተምር የአለም አስተሳሰን ግን የትእቢት የከፍታ የንቀትና ትምህክትኘነትን ስግብግብነትን፣ አስተሳሰብን ያራምዳል፡፡ በአለም አሰራር ትህትና ሽንፈትና ደካማነት ነው፡፡
• የየዋህነትና የብልጠት አካሄድ
የእግዚአብሔር መንግስት አስተሳሰብ ሃይልን ለክፉ ነገር ያለመጠቀም ውሳኔ ሲሆን በአለም ግን ብልጠትና አቋራጭ ተጠቅሞ ወደላይ ከፍ ማለትን የሚያበረታታ አሰራር ነው፡፡ የእግዚአብሔር መንግስት ሰው ስለ ደህንነቱ በእግዚአብሔር ላይ የሚደገፍበት ሲሆን የአለም አሰራር ግን ባለህ ሃይል እና ተሰሚነት ሁሉ ተጠቅመህ ሌላውን በመጣልና በማዋረድ ከፍ የማለት አስተሳሰብ ነው፡፡ በአለም አንተ ከፍ እንድትል ሌሎች መዋረድ አለባቸው፡፡
ስለዚህ ነው ጌታችን ኢየሱስ የእግዚአብሔር መንግስት ቀርባለችና ንስሃ ግቡ እያለ ይሰብክ የነበረው፡፡ በአለም አስተሳሰብ በእግዚአብሔር መንግስት ሊሳካልን አይችልም፡፡