አውቃለሁ እንደሚል ሰው የሚያስፈራ ሰው የለም፡፡ አውቃለሁ የሚል ሰው ለመማር ምንም ስፍራ የለውም፡፡ አውቃለሁ የሚል ሰው ለመማር ፈቃደኛ አይደለም፡፡ አውቃለሁ የሚል ሰው ለመሻሻል ምንም ቦታ የለውም፡፡ አውቃለሁ የሚል ሰው ማደግ አቁሟል፡፡ ሁሉንም አውቃለሁ የሚል ሰው ለመለወጥ ተስፋ የለውም፡፡
ለራሱ ጠቢብ የሆነ የሚምስለውን ሰው አየኸውን? ከእርሱ ይልቅ ለሰነፍ ተስፋ አለው። ምሳሌ 26፡12
ሁሉን አውቃለሁ ማለት የሚችል እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ ሁላችንም እየተማርን ነው፡፡ ለመማር እስከተዘጋጀን ድረስ ሁል ጊዜ እንማራለን፡፡ ለመማር እስከፈቀድን ድረስ የምንማራቸው እጅግ ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ እያንዳንዱ ሰው በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ በእውቀት ይበልጠናል፡፡ ከማንም ሰው ለመማር ፈቃደኛ ከሆንን ማንም ሰው ሊያስተምረንና በህይወታችን ላይ ዋጋን ሊጨምር ይችላል፡፡ ሁልጊዜ የሚማር ልብ ካለን በማንም ሰው አማካኝነት ለህይወታችን መለወጥ የሚጠቅም ቁልፍ ነገር ልንማር እንችላለን፡፡
ሰው ባወቀ መጠን የሚያውቀው ማወቅ የሚገባውን ያህል አንደማያውቅ ነው፡፡
ማንም አንዳች የሚያውቅ ቢመስለው ሊያውቅ እንደሚገባው ገና አላወቀም፤ 1ኛ ቆሮንቶስ 8፡2